ቀጥታ፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ሌሎች የልማት መስኮችን መደገፍ እንዲችል ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ዶክተር ዓለሙ ስሜ

ወላይታ ሶዶ ፤ ጥር 7/2016 (ኢዜአ)፡-የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ  ሌሎች የልማት መስኮችን ደግፎ የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ገለጹ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው አጋማሽ የሥራ አፈጻጸም ግምገማውን በወላይታ ሶዶ እያካሄደ ነው። 


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በዘርፉ እስካሁን የተከናወኑትንና የተሳኩ ጉዳዮችን በማጠናከር ለአገራዊው ብልጽግና ጉዞ ስኬት ርብርብ እየተደረገ ነው።

“ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ የምትሰራባቸው ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ቱሪዝምና ቴክኖሎጂ መስኮች ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የደም ሥራቸው ነው” ብለዋል።

ዘርፉ ምርቱንም ሸቀጦችንም ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲሳካና የአገሪቱ ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየታየ መምጣቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አማራጮች የማቅረብ አቅም እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን “ከእዳ ወደ ምንዳ” የሚያሸጋግሩ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ያመለከቱት ዶክተር ዓለሙ፣ ለዚህም የሎጀስቲክስ አገልግሎቱን ለማሳለጥ ያስችላል የተባለውን የወደብ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርገው የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር መፈረሙን በማሳያነት አቅርበዋል።

ይህም የትራንስፖርት ዘርፉን ወደተሻለ ደረጃ የሚያደርስና የወደብ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ የመግባቢያ ስምምነቱ ዲፕሎማሲው ጥበብ በተሞላበት መንገድ በመመራቱ የተገኘ ውጤት መሆኑንም አብራርተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ከመሆኑ አንጻር ይህን ሀብቱን ተጠቅሞ ለመበልጸግ የትራንስፖርት ዘርፉ እገዛ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።


 

“የብልጽግና፣ የመቻቻል፣ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት የሆነ ክልል ለመፍጠር ያሉትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን የበለጠ በማልማትና ጥቅም ላይ በማዋል በጋራ ለማደግ በሚደረገው ጉዞ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ ሚና የጎላ ነው” ብለዋል።

ከክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ የሚያቀርባቸውን ቡና፣ ፍራፍሬ፣ የዓሣና ሌሎች ምርቶች በጥራትና በፍጥነት ለማቅረብ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም ከሚኒስቴሩ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘርፉ ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ በመሆኑ በጅምር ላይ የሚገኙ የመንገድ ሥራዎች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ድጋፍ እንዲደረግ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።

በግምገማው ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርትና መሠረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ የክልሎችና የከተማ  አስተዳደሮች የዘርፉ ሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም