በኢኮኖሚ የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ የባህር በርን የማግኘት ጉዳይ ወሳኝ ነው -መምህራንና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ - ኢዜአ አማርኛ
በኢኮኖሚ የበለፀገች ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ የባህር በርን የማግኘት ጉዳይ ወሳኝ ነው -መምህራንና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ
ቦንጋ፤ ጥር 07/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማጠናከር የባህር በርን የማግኘት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን መምህራንና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ገለጹ፡፡
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በቦንጋ ከተማ አስተዳደር የቢሻው ወልደ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር አሸብር ሙላቱ፣ ኢትዮጵያ የጥንት ስልጣኔ የነበራት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
ለዚህ እንደምክንያት የሚያነሱት ደግሞ የባህር በር ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው አንድ ሀገር የባህር በር ሲኖረው በኢኮኖሚ የበለፀገ፣ የፖለቲካ ተሰሚነቱ ከፍ ያለ ይሆናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር አካባቢ ባይተዋር ሆና ለበርካታ አስርት ዓመታት መቆየቷን ጠቁመው፣ አሁን መንግስት የባህር በርን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ መነሳቱ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህር በር ጉዳይ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ የዘለቀ መሆኑን አንስተው በቅርቡ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ከጠቀሜታው አንጻር ለተፈጻሚነቱ ሁሉም መትጋት አለበት ብለዋል።
የባህር በር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሀገራት ጭምር ተባብሮ ለማደግና ጠንካራ አካባቢን ለመፍጠር ትልቅ እገዛ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በአካባቢው ተፅኖ ፈጣሪ መሆኗን ያነሱት በትምህርት ቤቱ የጂኦግራፊ መምህሩ ታደሰ ዳቦላ ናቸው።
ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የሀገር ሚስጥርን ለመጠበቅ የወደብ ባለቤት መሆን አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ ስምምነቱ ከግብ እንዲደርስ የትኛውንም አይነት ሰላማዊ አካሄድ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
የሚፈጠሩ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር በር አልባ መሆን በኢኮኖሚዋና በወጪ ገቢ ንግዷ ላይ እያሳደረ ያለው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የሚዲያ ባለሙያው አቶ ፀጋዬ ወልደማሪያም ናቸው፡፡
አገሪቷ አሁን የደረሰችበት እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው የባህር በር የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ናት ብለዋል።
በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ዘመኑን የሚመጥን አካሄድ መሆኑን አንስተው፣ ለዚህም ኢትዮጵያ አቅም እንዳላት ገልፀዋል።
የባህር በር ጥያቄው በትውልዱ ዘንድ ሲነሳ የቆየ መሆኑን ገልፀው መንግስት የጀመረው አካሄድ ከግብ እንዲደርስ እጅ ለእጅ በመያያዝ መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።