የኢትዮጵያን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት የሚከላከሉ ትጥቆችን መታጠቃችን ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት የሚከላከሉ ትጥቆችን መታጠቃችን ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ጥር 07/2016(ኢዜአ)፦ የሀገራችንን የአየር ክልል ከማንኛውም ጥቃት ሊከላከሉ የሚችሉ ዘመናዊ የውጊያ ትጥቆችን መታጠቃችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ።
የኢፌዴሪ አየር ሀይል እጅግ ዘመናዊ የሆነውን የመጀመሪያ ዙር የsu-30 ተዋጊ ጀቶችንና የስትራቴጂክ ሰው አልባ ተዋጊ አውሮፕላኖችን መታጠቁን ተመላክቷል።
በዚሁ ርክክብ ላይ የተገኙት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ በአለማችን ላይ ተመራጭ የሆኑትን የsu-30 እና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላን ባለቤት መሆናችን በሀገራችን ላይ ሊቃጡ የሚሞከሩ ጥቃቶችን ለማክሸፍ ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የ5ኛ ትውልድ አካል የሆኑት ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖችና የስትራቴጂክ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አየር ሀይሉን የማዘመን አንዱ አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አንጋፋው የኢትዮጵያ አየር ሀይል በአፍሪካ በውጊያ አቅሙ፣ በጀግንነቱና በትጥቁ የነበረውን ዝና ዘመኑ በሚጠይቀው መልኩ ለማዘመን እየተሰሩ ያሉት ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገለፁት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ፣ ዘመን ተሻጋሪ የአየር ሀይል የመገንባት እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ፣ አየር ሀይሉ በሰለጠነ የሰው ሀይል ፣ በትጥቅና በውጊያ መሰረተ ልማት መጠናከሩን ጠቁመዋል።
ተቋሙ የተረከባቸው ዘመናዊ የጦር ጀቶች በተመሳሳይ ጊዜ በአየርና በምድር ላይ ያለ የጠላት ታርጌትን ማውደም የሚችል መሆኑን ጠቁመው ዘመናዊ የሰው አልባ አውሮፕላኖችም የጠላትን ዒላማ የማይስቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ አየር ሀይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለጠቅላይ ኤታማዦሩ ሹሙና ለእንግዶች ተዋጊ ጀቱን በማብረር የተለያዩ የአየር ላይ ትእይንቶችን ማሳየታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።