በመስኖ ልማት ኑሯችን እየተለወጠ ነው-የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በመስኖ ልማት ኑሯችን እየተለወጠ ነው-የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች
ኦሞራቴ ፤ ጥር 7/2016(ኢዜአ)፦በመንግስት በተደረገላቸው ድጋፍ የኦሞ ወንዝን በመጥለፍ የጀመሩት የመስኖ ልማት ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች ገለጹ።
በመስኖ ልማቱ ከ800 በላይ የወረዳው አርብቶ አደሮች በመሳተፍ የገቢ አቅማቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ ተነግሯል።
በዳሰነች ወረዳ የሎበት ቀበሌ ሞዴል አርብቶ አደር ሎቆልማ አኳብሎ ለኢዜአ እንዳሉት ከሌሎች የአካባቢው አርብቶ አደሮች ጋር በመሆን በ5 ሄክታር መሬት ላይ ማሽላ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ሀብሀብን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችና የጓሮ አትክልቶችን በመስኖ እያለሙ ነው።
የመስኖ ልማት ከጀመሩ ወዲህ ኑሯቸው በእጅጉ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለፁት አርብቶ አደሩ ከዚህ ቀደም ከብቶቻቸውን ይዘው ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የሚያጠፉትን ጊዜም መቆጠብ እንደቻሉ ገልፀዋል።
የአካባቢው አርብቶ አደሮች ለግጦሽ ሳር ፍለጋ ለወራት ያህል ከቤተሰብ ርቀው እንደሚሄዱ አስታውሰው በዚህም ማህበራዊ ግኑኝነታቸው ጠንካራ እንዳልነበር ገልፀዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት በተደረገላቸው ድጋፍ በአካባቢያቸው የሚገኘውን የኦሞ ወንዝ በመጥለፍ የጀመሩት የፍራፍሬና የአትክልት ልማት ችግሮቹን ከመፍታት ባለፈ በኢኮኖሚው ተጠቃሚ በማድረግ ኑሯቸው እየተለወጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
እንደ አርብቶ አደር ሎቆልማ ገለፃ ከዚህ ቀደም በደሳሳ ጎጆ ይኖሩ የነበረ ሲሆን የመስኖ ልማት ከጀመሩ ወዲህ ከሚያገኙት የምርት ሽያጭ የቀለብ ፍጆታቸውን ሸፍነው ቆርቆሮ ቤት መስራት ችለዋል ።
ልጆቻቸው ከዚህ ቀደም ከትምህርት ይልቅ ከብቶችን በማሰማራት ላይ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ እንደነበር ገልፀው፤ አሁን የእንስሳት መኖ በአካባቢው ስለሚለማ ልጆቻቸው ያለምንም ሀሳብና ጭንቀት በተረጋጋ ሁኔታ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርብቶ አደር ሙዶኮር ኖቶንጉሌ"ከዚህ ቀደም በአካባቢው የመስኖ ልማት ባለመታወቁ ለም አፈርና የኦሞ ወንዝ እያለ ማልማት ባለመቻላችን ለችግር ስንዳረግ ነበር" ብለዋል።
"ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመስኖ ልማቱ እንድንሳተፍ መንግስት ባመቻቸልን እድል መሰረት የጥራ ጥሬ ሰብሎችን፣ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን እያለማን እንገኛለን" ሲሉም ገልጸዋል።
የመስኖ ልማቱ ከእንሳስት እርባታው ባሻገር ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደፈጠረላቸው ገልፀው በዚህም ኑሯቸው በእጅጉ እየተለወጠ መምጣቱን ተናግረዋል።
የዳሰነች ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መስፍን እኩሞ በወረዳው በዘንድሮ አመት 441 ሄክታር መሬት በመስኖ በመታገዝ በሰብል፣በፍራፍሬና በጓሮ አትክልት እየለማ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ከሰብል ማሽላና ስንዴ፣ ከፍራፍሬ ደግሞ ፓፓያ፣ ሙዝና ሀብሀብ ከጓሮ አትክልት ደግሞ ቀይ ሽንኩርት፣ቲማቲምና ሌሎችንም እያለሙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመስኖ ልማቱ ከ800 በላይ የወረዳው አርብቶ አደሮች በመሳተፍ የገቢ አቅማቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የአካባቢው አርብቶ አደሮች በየጊዜው በመስኖ ልማቱ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
ይህንኑ ተከትሎ ለመስኖ ስራው የሚውሉ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ውስንነት መከሰቱን ጠቁመው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
አካባቢው ለእርሻ ምቹ መሆኑን አንስተው የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር በፀሐይ ሐይልና በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች እንዲቀርቡ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።