ከ200 በላይ ነጋዴዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር በማይጨው ከተማ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
ከ200 በላይ ነጋዴዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር በማይጨው ከተማ ተከፈተ
ማይጨው ፤ጥር 07 /2016(ኢዜአ) ፦በማይጨው ከተማ ከ200 በላይ ነጋዴዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ ኤግዚቪሽንና ባዛር ተከፈተ።
በማይጨው ከተማ የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ200 በላይ ነጋዴዎች የተሳተፉበት አገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፈተ።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ በአካባቢው ተቀዛቅዞ የቆየውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
ኤግዚቢሽንና ባዛሩን የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስና የማይጨው ከተማ ከንቲባ አቶ የማነ ንጉስ ከፍተውታል።
በወቅቱም የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የተከፈተው ኤግዚቢሽንና ባዛር ተቀዛቅዞ የቆየውን ኢኮኖሚ ከማነቃቃት ባለፈ አንድነታችንና ባህላችንን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል።
የባዛሩ አስተባባሪ አቶ አበባ እያሱ እንደተናገሩት ከትግራይና ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡት 210 ነጋዴዎች በኤግዚቪሽንና ባዛሩ ላይ እየተሳተፉ ነው ብለዋል።
በዚህም ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ ይንቀሳቀስበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአዲስ አበባ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ፣ የልጆች ልብስና የቤት እቃዎችን ይዘው የመጡት ወጣት አብዲ ሓበሻና ትንቢት ደምሴ በማይጨው ከተማ የጥምቀት በዓል በድምቀት ስለሚከበር የተሻለ ግብይትን ለመፈፀም መምጣታቸውን ገልፀዋል።
ባዛሩ ጥራት ያላቸው እቃዎች በተሻለ ዋጋ እንድናገኝ ያግዛል ያሉት ደግሞ በኤግዚቢሽኑ ያገኘናቸው የማይጨው ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሓዳስ ስዩምና አቶ ካሕሳይ ከላሊ ናቸው።
በኤግዚቢሽንና ባዛሩ የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ፣ የማይጨው ከተማ ከንቲባ አቶ የማነ ንጉስን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
እግዚቢሽንና ባዛሩ ለአስር ቀናት እንደሚቆይም ከባዛሩ አስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።