ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያከናወነቻቸው ተግባራት በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ያላትን ጉልህ ስፍራ የሚያሳዩ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያከናወነቻቸው ተግባራት በዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ያላትን ጉልህ ስፍራ የሚያሳዩ መሆናቸውን በተለያዩ አገራት የሚሰሩ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን፤ ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ" በሚል ሀሳብ ያዘጋጀው የዲፕሎማሲ ሳምንት ስድስተኛ ቀኑን ይዟል፡፡

ኢትዮጵያ ከንግስት ሳባ ሥርዓተ መንግስት ጀምሮ በፈጠረችው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበራትን ገናና ሥም ለዘመናት አስጠብቃ ቆይታለች፡፡

በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የዲፕሎማሲ ታሪኳን የሚመጥን የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ስራዎችን እያከናወነች ነው፡፡

አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ከአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች ነፃ ሳይወጡ ኢትዮጵያ በ1943 ዓ.ም በእንግሊዝ ኤምባሲ ከፍታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከመንግስታቱ ማህበር /ሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ አፍሪካ ህብረት ከአባልነት እስከ መስረታ የነቃ ተሳትፎ አድርጋለች ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ሥራዎች በባለብዙ ወገን ዘርፍ ተሳትፎ በዲፕሎማሲው መስክ የነበራትን ጉልህ ሥፍራ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ማህበር አባል፤  የገለልተኛ ሀገሮች ድርጅት መስራት፣ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ የብሪክስ አባል ሆና የተመረጠች ሀገር መሆኗን አስታውሰዋል፡፡


 

በአልጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ ዛሬ ላይ የምናውቃቸው ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች በሙሉ ኢትዮጵያ በአባልነት ወይም በመስራችነት የተሳተፈችባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው በአይነቱ ልዩ የሆነ የዲፕሎማሲ ሳምንት የኢትዮጵያ ታላቅነትና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የነበራትን ጉልህ ሚና ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ሥራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወይም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሚያራምዱ መሪዎች ብቻ የተከበበ ሳይሆን ማህበረሰቡን የሚያሳትፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በመሆኑም ዘመኑን የዋጀ የውጭ ግንኙነት ለመፍጠር በመንግስትና ዲፕሎማቶች ብቻ የታጠረውን ዲፕሎማሲ ሁሉን አቀፍ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡


 

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሌንጮ ባቲ፤ በዓለም ላይ ብዙ የላቲን አሜሪካ፣ ካሪቢያን፣ ኤዥያ እና የአፍሪካ ሀገሮች ሀገር ሳይሆኑ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ያለ ስምና ዝና እንደነበራት ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ በየዘመናቱ የነበሩ መሪዎች ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለዓለም አስተዋውቀዋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባለፉት አምስት ዓመታት በብሪክስ፣ በአረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያ ስም ከፍ ማድረጋቸው ገልጸዋል፡፡

በቀጣናዊ ሰላምና ትብብር በተለይም ከኤርትራ ጋር በፈጠሩት ሰላም የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር ብርሀኑ ጸጋዬ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ የዲፕሎማሲ ሥኬቶች የመሪዎችን ቁርጠኝነት ማሳያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነትና ተቀባይነት ለማጎልበት ከሀገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

 

   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም