ጥምቀት የሚከበርበት ስፍራ የጥገናና የእድሳት ስራ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ጥምቀት የሚከበርበት ስፍራ የጥገናና የእድሳት ስራ ተጠናቀቀ

ጎንደር ፤ ጥር 7/2016 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ ጥምቀት የሚከበርበት የአጼ ፋሲለ ደስ ባህረ ጥምቀቱ ስፍራ የጥገናና የእድሳት ስራ ተጠናቆ ጥምቀተ ባህሩን ውሃ የመሙላት ስራ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ዮናስ ይትባረክ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ጥምቀተ ባህሩ የውሃ ስርገት እንዳያጋጥመው በቅርስ ጥገና ባለሙያዎች ሲካሄድ የቆየው የጥገና ስራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡
ለአንድ ወር ያህል ሲካሄድ የቆየው የጥገና እና እድሳት ስራም ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቁ አሁን ላይ ጥምቀተ ባህሩን በውሃ የመሙላት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ጥምቀተ ባህሩ 25 ሜትር በ50 ሜትር ስፋት ሲኖረው ጥልቀቱ ደግሞ እስከ ሁለት ሜትር ከ50 ስፋት እንዳለው ጠቁመው፤ ውሃ የመያዝ አቅሙ ደግሞ 189 ሺህ ሜትር ኪዩብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በታቦታት ማደሪያና መዋያ ስፍራዎች በቂ የጽዳትና ውበት ስራዎች መከናወኑን አመልክተው፤ የኤሌትሪክ መስመር ዝርጋታ ስራም መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ስርዓተ ጥምቀቱን በቅርበት ለመከታተል የሚያስችሉ የእንግዶች ማስተናገጃ ቋሚና ጊዚያዊ መቀመጫዎችም በበቂ መጠን መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በዓሉን ለመታደም የሚመጡ የእምነቱ ተከታዮችና እንግዶች ለሚገጥማቸው ድንገተኛ የጤና ችግር የህክምና እርዳታ የሚሰጥ ጊዚያዊ ክሊኒክ መቋቋሙንም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በበዓሉ ስፍራ ሊያጋጥም የሚችለውን የኔት ወርክ መጨናነቅ ለማስቀረት ኢትዮ ቴሌኮም ጊዚያዊ የሞባይል ኔት ወርክ ማቀባበያ ተከላ ስራ ማካሄዱን የመምሪያ ሃላፊው ገልጸዋል፡፡