በአርባ ምንጭ ከተማ በ17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነባው አደባባይ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
በአርባ ምንጭ ከተማ በ17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የተገነባው አደባባይ ተመረቀ
አርባ ምንጭ፤ ጥር 06/2016 (ኢዜአ) አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአርባ ምንጭ ከተማ ኩልፎ ሰፈር በ17 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ያስገነባው አደባባይ በዛሬዉ ዕለት ተመርቋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በሃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራ ጎን ለጎን በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የተለያዩ ማህበረሰብን የሚጠቅሙ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ በዛሬው ዕለት የተመረቀው ከ17 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን አደባባይ አንስተዋል።
ይህም አርባ ምንጭ ከተማና አካባቢዋ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ፀጋ ከማስተዋወቅም በላይ በማልማት ለከተማውም ሆነ ለሀገር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ድርሻ እንዲወጣ ታስቦ መገንባቱን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የፈረመችውን የዘላቂ ልማት ስምምነት ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም ለዚሁ ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በከተማው በተለምዶ ኩልፎ ሰፈር ላይ ገንብቶ ለምረቃ ያበቃው አደባባይ በከተማ ልማት ዘርፍ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
አደባባዩ ለከተማዋ ገጽታ ልዩ ውበትና ድምቀት የሚጨምር መሆኑን አንስተው አካባቢውና ከተማው ያለውን ዕምቅ የቱሪዝምና ሌሎች ሀብቶች በጉልህ በሚያሳይ መልኩ የተገነባ መሆኑ ለየት እንዳደረገውም ገልጸዋል።
"በተለይም አካባቢው በቱሪዝም፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በዓሣ ምርት ረገድ ያለውን አቅም የሚያስገነዝብ ሆኖ መገንባቱ አስፈላጊውን ሁሉ በተቀናጀ መንገድ በመከወን ለከተማችን ዕድገት የበኩላችን እንድንወጣ አነሳስቶናል" ብለዋል።
አደባባዩ ከመገንባቱ በፊት አካባቢው ያልለማና ለአይን እይታ ማራኪ እንዳልነበር የተናገሩት በአርባ ምንጭ ከተማ የኩልፎ ሰፈር ነዋሪ አቶ አንጁሎ ካምቦ ናቸው ።
''አሁን ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው ይህ አደባባይ የሰፈሩን ገጽታ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ገልጸው የሚያስደስት ተግባር ነው'' ብለዋል።
በምረቃ ስነ-ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው፣ የጋሞ ዞን እና የአርባ ምንጭ ከተማ የሥራ ሃላፊዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።