ቀጥታ፡

ለጤና ተቋማት ከ15 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ደሴ፤  ጥር 6 /2016(ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

የማህበሩ ዳይሬክተር ዶክተር አለማየሁ መኮንን እንደገለጹት፤ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ጤና ተቋማት በጋራ መልሶ በማቋቋም ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል፡፡


 

ማህበሩ አጋር አካላትን አስተባብሮ ጭምር በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች በጦርነቱ ለተጎዱ ጤና ተቋማት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ዛሬ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ከድጋፉ መካከል አልትራ ሳውድ ማሽን፣ ኬሚስትሪ ማሽን፣ የህጻናት ማሞቂያ ማሽን፣ የደም መለኪያና መመርመሪያ ማሽን፣ ልዩ ልዩ አልጋዎችና ሌሎችም ይገኙበታል።

ድጋፉ ለ30 ጤና ጣቢያዎችና ለ70 ጤና ኬላዎች የሚከፋፈል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሌሎች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ብርሃን ሀይሌ በበኩላቸው፤ በሰሜኑ ጦርነት ጤና ተቋማት ላይ ጉዳት በመድረሱ መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡


 

በዚህም የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ዛሬ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፤ ለ15 ጤና ጣቢያዎችና ለ35 ጤና ኬላዎች ይከፋፈላል ብለዋል።

ድጋፉም የህክምና ተቋማትን አገልግሎት ለማሻሻል ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፤ ለተደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።

ዛሬ የተደረገልን ድጋፍ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ከማገዙ ባለፈ ጤና ተቋማት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ እድል የሚፈጥር ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ ናቸው፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ስነ ሰርዓት ላይ የዞንና የወረዳ አመራር አባላትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም