በጎንደር ጥምቀት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር የድርሻችንን እንወጣለን - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ጥምቀት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር የድርሻችንን እንወጣለን - ነዋሪዎች
ጎንደር፤ጥር 6/2016 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የከተማው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በጎንደር ጥምቀት የቆየ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ማስተናገድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ ምክክር ተደርጓል፡፡
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት የምስራች መላኩ፤ የጥምቀት በዓል በተለይም በወጣቱ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ተዘጋጅተናል ብላለች።
በከተማው ተፈጥሮ የነበረው የሰላም መደፍረስ በአሁኑ ወቅት መረጋጋቱን ጠቁማ፤ በዓሉ በሰላም እንዲከበርና እንግዶችን ተቀብሎ በሰላም ለማስተናገድ እየሰራን ነው ስትል ተናግራለች፡፡
ሌላው ነዋሪ አቶ ገበያው ተረፈ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል እንደከዚህ ቀደሙ በድምቀት እንዲከበር የድርሻዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል፡፡
ጥምቀት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ ሲከበር የቆየ ዘመን ተሻጋሪ እሴት መሆኑን አመልክተው፤ በዚህ ዓመትም የቀደመ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ አግባብ እንዲከበር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።
ጎንደር ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ በመሆኑም በርካታ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ቱሪስቶች ጥምቀትን ለመታደም ይመጣሉ ያሉት ደግሞ አቶ ተስፉ ይርጋ ናቸው።
በዘንድሮ ዓመት ጥምቀት በደመቀ ሁኔታ በሰላም እንዲከበር የእምነቱ ተከታዮችና የከተማው ነዋሪዎች ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም አጥብቀን እየሰራን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዓሉ ደምቆ እንዲከበር በተለይም የሰላም ስራዎችን ለማጠናከር እንዲቻል ታልሞ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው ያሉት ደግሞ በከተማው የዞብል ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገብረሚካኤል አየልኝ ናቸው፡፡
በዓሉ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር ህዝቡ በሰፈር፣ በቀበሌና በቀጣና ደረጃ ሰላሙን ለመጠበቅ እንዲቻል የጋራ መግባባትና አቋም ላይ የተደረሰበት መድረክ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል በሰላምና በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር የተቋቋሙት ዐብይና ንዑሳን ኮሚቴዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
የጥምቀት በዓል የከተማውን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ፍሰት በመጨመር የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰው፤ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ህዝቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር የጀመረው የሰላም ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል፡፡
የጎንደር ልዩ መለያና መገለጫ የሆነው የጥምቀት በዓል ለከተማው የንግድና የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመልክተዋል።
በከተማው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓቱን በጠበቀ መንገድ በሚከበረው የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ለመታደም የአገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡