ዞኑ ያለውን አቅም በመጠቀም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዞኑ ያለውን አቅም በመጠቀም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ነው
ቦንጋ ፤ጥር 6/2016 (ኢዜአ)፦ በቦክስ፣ በአትሌቲክስና በሌሎች የስፖርት ዘርፎች ላይ በዞኑ ያለውን አቅም በመጠቀም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።
የካፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ አምቦ ስፖርት በኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በዞኑ ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በትኩረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
ዞኑ ከዚህ ቀደም በቦክስ ስፖርት ጥሩ እንቅስቃሴና ተወዳዳሪ ስፖርተኞች የነበሩት ቢሆንም በትኩረት ማነስና በአሰልጣኝ እጦት ምክንያት መቀዛቀዙን ተናግረዋል።
ከቦክሱም ባሻገር በአለም አቀፍ መድረኮች ሀገራቸውን የወከሉ አትሌቶችና ብስክሌተኞች የወጡበት አካባቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዞኑ ያለውን አቅም በመጠቀም በተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች በግለሰቦችና በፕሮጀክት የታቀፉ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያግዙ ተስፋ ሰጪ ጅምር ስራዎች አሉ ብለዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቦክሰኛ ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ካሳሁን በቀለ በበኩሉ በ1990 ዓም በምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ የቦክስ ሻምፒዮና ላይ የብር ሜዳሊያ ተሸለሚ መሆኑን ተናግሯል።
አሁን የኢንተርናሽናል ቦክስ ፌደሬሽን አባል ሆኖ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በመዘዋወር ቦክስ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ገልፆ ልምዱን በማካፈልና በማሰልጠን በአካባቢው ብሎም በሃገር ደረጃ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚጠበቅበትን ለመወጣት እየሰራ እንደሆነ ተናግሯል።
በጂም ውስጥ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብረሃም ጌታቸው በበኩሉ ማእከሉ ከሱስ የፀዳ፣ በስፖርት የዳበረና በጥሩ ስነምግባር የታነፀ ዜጋ መፍጠር የሚል ዓላማ ይዞ የበኩሉን እየተወጣ ነው ብሏል።
አካባቢው የስፖርት ብቃትና ፍላጎት ያላቸው ስፖርተኞች መገኛ ቢሆንም ትኩረት አልተሰጠውም የሚለው ኢንስትራክተሩ ከተለያዩ ታዋቂ አሰልጣኞች ጋር በትብብር በመስራት ግቡን ለማሳካት እንደሚጥርም ገልጿል።
ስፖርት በጥሩ ስነምግባር የሚያንጽ፣ የሚያነቃና ጤናን ለመጠበቅ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን የገለፀው ደግሞ በማእከሉ ቦክስ የሚሰለጥነው ወጣት ሳምሶን አሸብር ነው።
በዞንና በክልል መድረኮች በተለያዩ ውድድሮች አካባቢውን ወክሎ ተወዳድሮ ውጤት እንዳመጣ ጠቅሶ በቀጣይ በቦክስ ብቁ ተወዳዳሪ የመሆን ራዕይ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጧል።
የኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ካሳሁን በቀለ ወደ ቦንጋ መምጣት ይበልጥ ተነሳሽነት እንደሚፈጥርላቸውና ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸውም ጠቁሟል።
ሌላኛዋ በማሰልጠኛ ማዕከሉ የጤና ሰልጣኝ የሆነችው አዳነች ሀጎስ በበኩሏ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች መሳተፍ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚያግዝ ተናግራለች።