ቀጥታ፡

የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ "የሀገሬ ጉዳይ የኔም ነው" የሚል መንፈስ በመፍጠር ሁሉም የሀገሩ አምባሳደር እንዲሆን ዕድል የፈጠረ ነው - አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ "የሀገሬ ጉዳይ የኔም ነው" የሚል መንፈስ በመፍጠር ሁሉም የሀገሩ አምባሳደር እንዲሆን ዕድል የፈጠረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ 

ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና ፖሊሲ ላይ ያላት አቋም ዛሬም የጸና መሆኑንም አምባሳደር መለስ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይና ዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጣ ውረድ የሚያስቃኘውና የነገውን አቅጣጫ የሚያመላክተው የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ አምስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ መድረኮች የነበራትን ጉልህ ሚና ለህዝብ ያሳየችበት ነው።

የውጭ ጉዳይና ዲፕሎማሲ ስራ የተወሰኑ ተቋማት ወይም የመሪዎች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ዜጎች ሁሉ መሳተፍ የሚችሉበት መሆኑን ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የተሳካ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋማዊ አደረጃጀት ይዞ ከተመሰረተበት ከ1900 ዓ.ም ጀምሮ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ያከናወናቸው ተግባራት በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጎብኝቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማሲ ሥራ በቅርበትም ሆነ በሩቅ የሚያውቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አውደ ርዕዩን በመጎብኘት ተጨማሪ ግብዓት ሰጥተውናል ብለዋል።

የዲፕሎማሲ ሳምንቱ አውደ ርዕይ የታሰበውን ዓላማ ያሳካ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር መለስ፤ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የነበራትን ሚናና የወደፊት ተሳትፎ ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።

ህፃናትና ወጣቶች እየተዝናኑ የሚማሩበት፤ ምሁራንና ተመራማሪዎች ለማጣቀሻነት የሚጠቀሙባቸው ጽሁፎችና መረጃዎች የቀረቡበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለወጠ የዓለም ሁኔታ ውስጥ ባልተለወጠ መንገድ በመጓዝ ዲፕሎማሲን ማሳካት እንደማይቻል ገልጸው፤ ዘመኑን የዋጀ የዲጅታል ዲፕሎማሲ መከተል ወሳኝ ነው ብለዋል።

የዲፕሎማሲ ሳምንቱን በየዓመቱ የማዘጋጀት እቅድ አለን ያሉት አምባሳደር መለስ፤ የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማሲ ሥራ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ዜጎች ሁሉ የሚሳተፉበት ነፃ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት እና የምርምር ተቋማት ተመራማሪዎች፣ ተማሪዎች፤ ወጣቶችና የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉም ዜጎች አውደ ርዕዩን በመጎብኘት የዲፕሎማሲው አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና ፖሊሲ ላይ ያላት አቋም ዛሬም የጸና መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአንዲት ቻይና ፖሊሲን ለረጅም ዓመታት ስታራምድ መቆየቷን አስታውሰው ይህ አቋሟ በዘመናት መካከል መንግስታት አፅንተው የያዙት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና ፖሊሲ ላይ ያላት አቋም ዛሬም የጸና መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም