የአፍሪካን የሰላምና የልማት ሽግግር ለማረጋገጥ ዘመኑን የዋጀ አፍሪካዊ ስርዓተ ትምህርትን መተግበር ያስፈልጋል-ሙሳ ፋኪ ማሃመት - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የሰላምና የልማት ሽግግር ለማረጋገጥ ዘመኑን የዋጀ አፍሪካዊ ስርዓተ ትምህርትን መተግበር ያስፈልጋል-ሙሳ ፋኪ ማሃመት
አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2016(ኢዜአ)፦ አፍሪካን የተረጋጋችና የበለጸገች አህጉር ለማድረግ ና ትውልድን ለመገንባት ዘመኑን የዋጀ አፍሪካዊ ስርዓተ ትምህርትን መተግበር እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ገለጹ።
የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት፣ የሕብረቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና አምባሳደሮች በተገኙበት የአፍሪካ ሕብረት 47ኛው የቋሚ ተወካዮች መደበኛ ስብሰባ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።
የዘንድሮው 47ኛው የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ገባኤ '21ኛው ክፍለ ዘመንን የዋጀ ትምህርት ለአፍሪካ' በሚል መሪ ሀሳብ በትምህርት ዘርፍ ላይ በማተኮር ከአንድ ወር በኋላ ይካሄዳል።
መሪ ቃሉ በአህጉሪቱ አካታች፣ ዘመን ተሻጋሪ፣ ጥራት ያለው እና ፋይዳ ተኮር ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ ዘላቂነት ያለው ስርዓተ ትምህርት መገንባት ላይ ያተኮረ ነው።
ሙሳ ፋኪ ማሃመት እንዳሉት፥ በአፍሪካ የተከሰቱ ግጭቶች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለዚህ ስኬት የሀገራት አንድነትና ትብብር ወሳኝ ነው።
የአባል ሀገራት ተወካይ አምባሳደሮችን ያቀፈው የሕብረቱ ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ፥ የሕብረቱ ስብሰባ ይዘቶችን በማርቀቅ ብሎም የጋራ መግባባት እንዲደርስ ቁልፍ ሚና ያለው አካል መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚቴው በስብሰባው መልከ ብዙ አህጉራዊ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮችን በትኩረት እንዲያጤንና ከአጀንዳ 2063 የተጣጣመ ውይይት እንዲኖረው አሳሰበዋል።
ኮሚቴው በአፍሪካ ሰላም፣ ልማትና ትስስርን ዕውን ለማድረግ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ምክክር በማድረግ በሁነኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ የውሳኔ ሀሳቦችን እንዲያቀርብም ነው አቅጣጫ ያስቀመጡት።
ለዚህም እንደ አህጉር ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ የተሻለ ነገን ለመፍጠር በሚያስችሉ አጀንዳዎች ለመምከር ወቅቱን ያገናዘቡ ሪፖርቶች እንደሚጠበቁ አመልክተዋል።
ለአብነትም የባለብዙ ወገን ጉዳዮች፣ የሕብረቱ ተቋማዊ ሪፎርም፣ የቀጣይ የሕብረቱ መሪዎች ምርጫ እና መሰል ጉዳዮችን ጠቅሰዋል።
ኮሚቴው መረጃዎቹን፣ ምክክሮቹንና የውሳኔ ሀሳቦቹን በፖለቲካዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ትክክለኛ ምስል በሚሰጡ አግባብ ማዘጋጀት እንዳለበት አንስተዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ መሪ ቃል በትምህርት ላይ ማተኮሩ ወጣቶችን በሳይንሳዊና ቴክኒካዊ ክህሎቶች በማብቃት አምራች ኃይል መፍጠርና አህጉራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ዓላማ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
በአፍሪካ አህጉራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ፣ ምርታማ እና ለሁሉም የምትመች አህጉር ለማድረግ ዘመኑን የዋጀ አፍሪካዊ ስርዓተ ትምህርትን መተግበር እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።
በመሆኑም ኮሚቴው በአፍሪካ የስርዓተ ትምህርት ሪፎርም ለማድረግ እና በዘርፉ ላይ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ጠቃሚ የውሳኔ ሀሳቦችን ለስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ማቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።
የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር አምባሳደር የሱፍ አሱማኒ፥ በስብሰባው ዓመታዊ ሪፖርቶች፣ የሕብረቱ ቁልፍ ተቋማት ሪፎርም ሂደት እንዲሁም የ2063 አጀንዳ የ10 ዓመት አፈጻጸም ይዳሰሳል ብለዋል።
በተመሳሳይ የ2063 አጀንዳ የቀጣይ 20 ዓመታት ዕቅድ እንዲሁም የ2024 መሪ ሃሳብ በሆነው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዙሪያ በጥልቀት ተወያይቶ የውሳኔ ሀሳቡን ለስራ አስፈጻሚዎች እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
ዛሬ በይፋ የተከፈተው 47ኛው የአፍሪካ ሕብረት የቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ ስብሰባ እስከ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ይቀጥላል።
44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ የፊታችን የካቲት 5 እና 6 ቀን እንዲሁም 37ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይደረጋል።