ቀጥታ፡

የከተራ እና የጥምቀት በዓል በደመቀና በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር በጎ ፈቃደኞች ቅድመ ዝግጅት ስራ አጠናቀዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2016 (ኢዜአ)፦በመዲናዋ የከተራ እና የጥምቀት በዓል በደመቀ ሁኔታ በሰላም እንዲከበር 15ሺህ  በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዝግጁ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በየዓመቱ ጥር 10 እና 11 የከተራና ጥምቀት በዓልን በድምቀት ያከብራሉ።


 

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች የከተራን እና የጥምቀት በዓልን ለማክበር የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በስፋት ይታደማሉ።

ኢዜአ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር እና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ  እያደረጉ ያለውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ቃለመጠይቅ አድርጓል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ይሁነኝ መሀመድ፤ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ኃይማኖታዊና ኃይማኖታዊ ያልሆኑ የአደባባይ ሁነቶች በደመቀ ሁኔታ ተከብረው ሰላማዊ በሆነ መንገድ  እንዲጠናቀቁ  ለማድረግ ማህበሩ በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውን ጠቁሟል።

የከተራን እና የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ  ይገኛል ብሏል።

በቅርቡም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ወጣቶች በማስተባበር በአሉን የሚከበርባቸውን ቦታዎች አስቀድሞ የማጽዳት  ስራ እንደሚከናወን ተናግሯል።

በዓላቶቹ በሚከበሩበት ወቅትም የጤና ችግር ለሚገጥማቸው አፋጣኝ እርዳታ እንዲያገኙ የሚያስችል ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር  እየተሰራ መሆኑን ጠቁሟል።

የከተራና ጥምቀት በዓል  በድምቀትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከብሮ እንዲያልፍ 15 ሺህ የሚሆኑ  በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች  ሁነቱን በማስተባበር ሂደት ላይ እንደሚሳተፉ ወጣት ይሁነኝ ገልጿል።

ወጣቱ በዓሉ በሰላምና በድምቀት ለማክበር የሚደረገውን ዝግጅት ህብረተሰቡ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርቧል።

ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ  በማስተባበር ሂደት ላይ ከሚሳተፉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት ለምለም ይትባረክ እና ዲያቆን እንዳለ ዓለሙ ይገኙበታል።


 

ወጣቶች በከተማዋ በአደባባይ ላይ የሚከናወኑ ልዩ ልዩ ኃይማኖታዊ እና ኃይማኖታዊ ያልሆኑ ዝግጅቶች በሚከበሩበት ወቅት ሰላማዊ በሆነ መልኩ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ በቀጣይ የሚከበረው የከተራ እና የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/  በታህሳስ 2012 ዓ.ም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም