ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣለን - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን የበኩላችንን ኃላፊነት እንወጣለን - ምሁራን
አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2016 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩን ስኬታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥናትና ምርምሮችን በማከናወን ለውጤታማነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ምሁራን ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት እና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
በዚህም ኮሚሽኑ የተሳታፊ ልየታን ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ወደ ዋነኛው የምክክር ምዕራፍ ለመሻገር መሰረት የሚሆኑ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር ይቻል ዘንድም ይህ ሀገራዊ የምክክር ሂደት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
ይህን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ምሁራን አገራዊ የምክክር ሂደቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ በህዝቦች ዘንድ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ውጤታማነቱ እንዲሆን በየሙያቸው ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የህግ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሙሉጌታ ጌጡ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ምርምሮችን በማከናወን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡
ስለሀገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነት፣ ስለሂደቱ እና ሌሎችም ቁልፍ ጉዳዮች ግንዛቤ የሚፈጥሩ አውደ ጥናቶች እንዲካሄዱ እንሰራለን ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ከበደ ገነቲ እንዳሉት፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ምሁራን ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡
እንደ ሀገር ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ ውይይትና ምክክር የተሻለው አማራጭ መሆኑን በጥናት በመደገፍ፣ የሀገራዊ ምክክሩን ጠቀሜታ ለህዝቡ ለማስረዳት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር በር የሚከፍት በመሆኑ ከምሁራን በተጨማሪ ወጣቶች፤ የሲቪክ ማህበራት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ሰሞኑን ለኢዜአ መግለጻቸው ይታወቃል።