ቀጥታ፡

በአፍሪካ በትምህርት ዘርፍ ላይ  መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ለምርታማ ትውልድ ግንባታ ወሳኝ ነው--ሙሳ ፋኪ ማሃመት

አዲስ አበባ፤ ጥር 6/2016 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ በትምህርት ዘርፍ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ለምርታማ ትውልድ ግንባታ ትልቅ ሚና እንዳለው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት ገለጹ።

ሊቀ መንበሩ ይህን ያሉት የአፍሪካ ሕብረት 47ኛው የቋሚ ተወካዮች መደበኛ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

የዘንድሮው 47ኛው የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ገባኤ '21ኛው ክፍለ ዘመንን የዋጀ ትምህርት በአፍሪካ' በሚል መሪ ሀሳብ በትምህርት ዘርፍ ላይ በማተኮር ከአንድ ወር በኋላ ይካሄዳል።


 

የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት እንዳሉት፥ በአፍሪካ የተከሰቱ ግጭቶች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለዚህ ስኬት የሀገራት አንድነትና ትብብር ወሳኝ ነው።

የአባል ሀገራት ተወካይ አምባሳደሮችን ያቀፈው የሕብረቱ ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ፥ የሕብረቱ ስብሰባ ይዘቶችን በማርቀቅ ብሎም የጋራ መግባባት እንዲደረስ ቁልፍ ሚና ያለው አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚቴው በስብሰባው መልከ ብዙ አህጉራዊ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮችን በትኩረት እንዲያጤንና ከአጀንዳ 2063 የተጣጣመ ውይይት እንዲኖረው አሳሰበዋል። 

ኮሚቴው በአፍሪካ ሰላም፣ ልማትና ትስስርን ዕውን ለማድረግ ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ ምክክር በማድረግ በሁነኛ መረጃ ላይ የተመሰረቱ የውሳኔ ሀሳቦችን እንዲያቀርብም ነው አቅጣጫ ያስቀመጡት።

ለዚህም እንደ አህጉር ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ የተሻለ ነገን ለመፍጠር በሚያስችሉ አጀንዳዎች ለመምከር ወቅቱን ያገናዘቡ ሪፖርቶች እንደሚጠበቁ አመልክተዋል።

ለአብነትም የባለብዙ ወገን ጉዳዮች፣ የሕብረቱ ተቋማዊ ሪፎርም፣ የቀጣይ የሕብረቱ መሪዎች ምርጫ እና መሰል ጉዳዮችን ጠቅሰዋል።

ኮሚቴው መረጃዎቹን፣ ምክክሮቹንና የውሳኔ ሀሳቦቹን በፖለቲካዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ትክክለኛ ምስል በሚሰጡ አግባብ ማዘጋጀት እንዳለበት አንስተዋል።

የዘንድሮው የአፍርካ ህብረት ጉባኤ መሪ ቃል በትምህርት ላይ ማተኮሩ አምራች ኃይል ለመፍጠርና ምቹ አህጉር ለመገንባት ትምህርት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ትልቅ ትርጉም ስላለው እንደሆነ ገልፀዋል።

በመሆኑም ኮሚቴው በአፍሪካ በትምህርት ላይ የሚደረግን ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት ጠቃሚ የውሳኔ ሀሳቦችን ለስራ አስፈፃሚዎች ስብሰባ ማቅረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም