ቀጥታ፡

የኢንዱስትሪ ፖሊሲው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና አለው - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ጥር 6/2016(ኢዜአ)፦ የኢንዱስትሪ ፖሊሲው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳለው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ አስታወቁ፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ላይ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋምቤላ ከተማ ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ በወቅቱ እንደገለጹት የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ መጀመሩ ተስፋ ሰጭ ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለውጡ በዘላቂነት እንዲቀጥል ለማስቻል በፖሊሲዎች፣ በሕግ ማዕቀፎች እና በመመሪያዎች ተደግፈው መሰራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

ይህን ተግባራዊ ለማድረግም በዘርፉ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻልና ፖሊሲዎችን በመከለስ መመሪያዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የኢንደስትሪ ልማትን ለማሳደግ በየአካባቢው ያሉትን ፀጋዎች መሰረት በማድረግ ባለሀብቶች በዘርፉ መዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ይሰራልም ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በክልሉ ያለውን ሃብት ከአምራች ሃይል ጋር በማሰናሰል ከተሰራ በአጭር ጊዜ ዕድገትና ብልፅግና ማረጋገጥ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች የተሻሻሉ የልማት ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ መጠነ ሰፊ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲያድግ በክልሉ ያሉ የኢንዱስትሪ አምራቾች ምቹ ሁኔታን እንዲያገኙ እንሰራለን ነው ያሉት።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አምቢሳ ያደታ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን ለማስቻል በክልሉ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተፈለገው ልክ ውጤት ማምጣት እንዲችል ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን በዝርዝር መፍታት ይጠበቃል ማለታቸውን ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም