ከተሞችን የተሻለ የመኖሪያና የስራ ማዕከላት የማድረጊያ ልምድ ቀስመናል - ከንቲባዎች - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞችን የተሻለ የመኖሪያና የስራ ማዕከላት የማድረጊያ ልምድ ቀስመናል - ከንቲባዎች
ድሬደዋ ፤ ጥር 5/2016 (ኢዜአ)፦ ከተሞችን የተሻለ የመኖሪያና የስራ ማዕከላት በማድረግ የአገር የብልፅግና ጉዞ ማሳኪያ የሚሆኑ ልምድና ተሞክሮ መቅሰማቸውን የተለያዩ ከተሞች ከንቲባዎች ተናገሩ።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፅህፈት ቤት ከኢትዮጵያ የከተሞች የትብብር መድረክ ጋር በመተባበር በድሬደዋ ለሁለት ቀናት ያካሄደው የልምድ ልውውጥ ዐውደ ጥናትና የስራ ጉብኝት ተጠናቋል።
በዐውደ ጥናቱ ላይ በከተሞች የገቢ አሰባሰብ፣በከተማ መሬት አያያዝና አጠቃቀም፣ በውበትና ፅዳት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በሰላምና የፀጥታ ስራዎች ላይ የተሻለ ልምድ ያላቸው ከተሞች ምርጥ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከንቲባዎቹ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በገቢ አሰባሰብ፣ በከተማ መሬትና ካዳስተር እንዲሁም ሰላምና ፀጥታን በመጠበቅ የተሰሩ ስራዎችን በመስክ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዚሁ ጊዜ የማይጨው ከተማ ከንቲባ የማነ ንጉስ እንደተናገሩት፤ ከልምድ ልውውጥ መድረኩ የቀሰሙትን መሠረታዊ ዕውቀቶችና ልምዶች በመቀመር የተሻለ ስራ እንሰራለን ብለዋል።
በተለይም የድሬዳዋ ከተማ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ የዘረጉት አሰራርና የአመራሩ ቁርጠኝነት የተሻለ ውጤት እንዲመጣና የህዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለስ እያከናወኑ ያሉት ተግባራት ለኛ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶናል ብለዋል።
የቦንጋ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃን መኮንን በበኩላቸው በልምድ ልውውጡ የቀሰሙት ዕውቀቶችን ወደ ተግባር በማውረድ የተጀመረውን አገራዊ የብልፅግና ጉዞ በከተሞች ዕውን እንዲሆን ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በተለይ የድሬዳዋ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሠሩት የሚገኙት ተግባራት እንደ አገር ለሚገኙ ወጣቶች በተሞክሮነት ሊቀሰም የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዱዓለም ጤናው በበኩላቸው ለሁለት ቀናት የተካሄደው የልምድ ልውውጥና የስራ ጉብኝት ከተሞች እርስ በርስ ተሞክሮዎችን የተለዋወጡበትና ለጋራ ችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ ለማምጣት እንዲችሉ አጋጣሚ የተፈጠረበት ነው ብለዋል።
የደረቅ ቆሻሻን በተሻለ መንገድ በማስወገድና ወደ ጥቅም በመለወጥ በአዲስ አበባ የተሠሩ ምርጥ ስራዎችና በባቱ ከተማ የሐይቅ ዳርቻዎችን በአግባቡ የማልማት ስራ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ከተነሱት መካከል መሆናቸውን አክለዋል።
ድሬደዋ በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰብ መሠረታዊ ለውጥ ፣ በስማርት ሲቲ ግንባታና በሌሎች መሠረታዊ ስራዎች የሌሎች ከተሞች ምርጥ ተሞክሮዎችም የቀረቡበትና ወሳኝ ውይይት የተካሄደበት መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈንታ ደጀን የተካሄደው የልምድ ልውውጥ ከተሞች እንደ አገር የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሰነቁት ራዕይ ዕውን እንዲሆን የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የሚታሰበውን ለማሳካት ደግሞ በመሬት ላይ የሚከናወኑ ስራዎችን በአግባቡ ማስተዳደርና መምራት ላይ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
በልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት ውይይት ላይም የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈንታ ደጀንና ሌሎች አመራሮችን ጨምሮ የበርካታ ከተሞች ከንቲባዎች፣ የከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።