ቀጥታ፡

የሰራዊቱን ግዳጅ የመፈፀም አቅም የመገንባቱ ሂደት የማያቋርጥ ተልዕኮ ነው - ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ

ጋምቤላ፤ ጥር 5/2016 (ኢዜአ)፡- የሰራዊቱን ግዳጅ የመፈፀም አቅም የመገንባት ሂደት የማያቋርጥ ተልዕኮ መሆኑን የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ አስታወቁ።

በዕዙ የ104ኛ ኮር የ35ኛ ዋልያ ክፍለ ጦር ሁለተኛ ዓመት የምስረታ አመታዊ በዓሉን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይትና በሌሎች ዝግጅቶች እያከበረ ነዉ።

በሀገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ዘውዱ በላይ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ሰራዊቱ የሚመጣ ጠላትን በመመከት የህዝቡን ሰላም እያስከበረ የሚገኝ ከህዝብ የወጣ ለህዝብ የሚቆም ሰራዊት ነዉ።


 

ሰራዊቱ ዋና ተልዕኮ የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር መሆኑን ጠቅሰው፤ ጦርነት ሲያጋጥመውም በአጠረ ጊዜ በድል በማጠናቀቅ ህዝቡንና የሀገርን ሠላም የመመለስ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሰራዊቱ የሚሰጠውን ግዳጅ በአግባቡ መፈፀም የሚያስችለዉን አቅም በመገንባት በኩል ስኬታማ ሰራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም የአቅም ግንባታው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኩዌይ ጆክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተሰማራበት የግዳጅ ቀጠና ሁሉ በድል እየተወጣ ያለ ሰራዊት ነዉ።

ሰራዊቱ ሀገሪቱ በየጊዜው የሚገጥሟትን ፈተናዎች በመመከት ለሉዓላዊነቷ መከበር ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገ ያለ የህዝብ ልጅ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይም ሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚገጥሟትን የተፈጥሮና ሰዉ ሰራሽ ችግሮች ሁሉ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል አኩሪ ድል እየተጎናፀፈ ያለ ሰራዊት መሆኑንም ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ለሰራዊቱ የሚያደርገዉን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።

በዕዙ የ104ኛ ኮር የ35ኛ ዋልያ ክፍለ ጦር የምስረታ አመታዊ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በጋምቤላ ከተማ እያከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም