ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ቅርሶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች የጥገና ስራ እየተካሄደ ነው 

መቀሌ፤ ጥር 5/2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃትና የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ የሚያስችል የቅርሶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች የጥገና ስራ በመካሄድ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ለክልሉ ቅርስና ቱሪዝም መዳረሻዎች ጥገና አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል። 

በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሃብታሙ አበበው እንደገለጹት፤ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ክልል ጉዳት የደረሰባቸው ቅርሶችና የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚያጠና ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

በትግራይ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችና የመዳረሻ ስፍራዎች የዳሰሳ ጥናት መደረጉን እና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ባለስልጣኑ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር  ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም አቶ ሃብታሙ ተናግረዋል።

በክልሉ ለሚከናወኑ የጥገናና መልሶ ማልማት ስራ ባለስልጣኑ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጉን በማከል።

ባለስልጣኑ የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማነቃቃት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማነቃቃት በመንግስት በጀት ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን አንስተው፤ ሁሉም በቅርስ ጥበቃና ልማት ላይ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ መላው ማህበረሰብም ቅርሶችን በመንከባከብና በማልማት ሃላፊነቱን እንዲወጣ አቶ ሃብታሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የብቃት ማረጋገጥ እና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ የማነ ገደሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች  የቱሪስቶች እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ ቆይቷል።

የቱሪዝም እንቅስቃሴውን መልሶ  ለማነቃቃትና ዘርፉ ማምጣት የሚገባውን ገቢ እንዲያመነጭ ታስቦ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ከአንድ ሳምንት በፊት በይፋ መከናወኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ለማነቃቃት መንግስት፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለ ሰቦች ሃላፊነታችውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

በዚህም የቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከቅርስ ባለስልጣን በመተባበር በአክሱም፣ ዓድዋ፣ ዓዲ ግራት ተምቤን፣ ገርዓልታ፣ ውቅሮና አልነጃሽ አካባቢዎች የሚገኙና ጥገና የሚያስፈልጋቸው 21 ቅርሶችና መዳረሻዎች  በአስቸኳይ የጥገናና ማልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ የማነ ገልጸዋል።

እነዚሁ የፌዴራል ተቋማት የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የጀመሩት ስልጠናና እና ሙያዊ ድጋፍም አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም