የፌዴራል ፖሊስ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ማኅበር እንዲጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴራል ፖሊስ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ማኅበር እንዲጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የቀድሞ ሠራዊት አባላት ማኅበር እንዲጠናከር አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማኅበር ውይይት አካሂዷል፡፡
የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ዘመናዊ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የቀድሞ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የካበተ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው በመሆኑ በተቋምና በሠራዊት አቅም ግንባታ ላይ የላቀ አበርክቶ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሀገራቸውን አገልግለው ጡረታ የወጡ አባላትን ማኅበሩ መሰብሰቡን ተናግረው፤ አባላቱ ያላቸውን ልምድና አቅም አሁን ላሉት የሠራዊት አባላት በማጋራት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሀገሩንና ሕዝቡን በስነ-ምግባር፣ በጀግንነት እና በሰብዓዊነት የሚያገለግል የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ የጀመረው የሪፎርም ሥራ በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘመናዊ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
የቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት አባላት ማኅበር እንዲጠናከርም አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል። ፌዴራል ፖሊስ ሕዝባዊነቱን ጠብቆ ሀገርን እና ሕዝብን የማገልገል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ኮሚሽነር ጀነራሉ አረጋግጠዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንስፔክተር ከድር አጎዢ፤ ማህበሩ ከተመሰረተ ሁለተኛ አመቱን ማስቆጠሩን ጠቅሰው አሁን ላይ 500 አባላት እንዳሉት ገልጸዋል።
የማህበሩ መቋቋም ዋነኛ አላማ በሙያና ክህሎት የፖሊስ ተቋምን በሚቻለው አቅም ለመደገፍ እንዲሁም ሀገራችንን እና ህዝባችንን ለማገልገል ነው ብለዋል።
ከማህበሩ አባላት መካከል አስተያየታቸውን የሰጡ የቀድሞ የፖሊስ አባላት በቀጣይ የተሻለ አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማህበር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሀገራቸውንና ሕዝብን አገልግለው በጡረታ በክብር የተሰናበቱ አባላት የገቢ ምንጭ የሚያስገኝ ሥራ ለመፈጠር ታስቦ የተቋቋመ ማህበር ነው።
በተጨማሪም በማህበራዊ ኑሮ የተጎዱት የማህበሩ አባላትን ለመርዳት በማሰብ ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 5978 በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ ሕጋዊ ፍቃድ ያገኘ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡