ቀጥታ፡

የወንጪ ደንዲ ፕሮጀክት በኢኮ-ቱሪዝም  በአፍሪካ ተምሳሌት መሆን የሚችል ነው-ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረ ማሪያም 

አዲስ አበባ ፣ጥር 5/2016(ኢዜአ)፡- የወንጪ ደንዲፕሮጀክት አካባቢውን ፣ባህሉንና  የህዝቡን አኗኗር በማሳየትና በማቀናጀት በኢኮ ቱሪዝም በአፍሪካ በተምሳሌትነት  ሊጠቀስ የሚችል ነው ሲሉ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም አስታወቁ፡፡

ፕሮፌሰር አለማየሁ ፕሮጀክቱን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት በሃይቁ አቀማመጥ እና  ድንቅ ተፈጥሯዊ ውበት ተደምሜያለሁ ብለዋል፡፡

በተለይ ከሀገሩ ርቆ የቆየ ዳያስፖራ ይህን መሰል ቦታ በማየት ለሃገሩ መቆርቆር እና ስለሃገሩ መናገር ይችላል ያሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ ኢትዮጵያ ይሄ ብቻም ሳይሆን ሌሎች መዳረሻዎችም እንዳሏት መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡


 

መሰል ቦታዎችን በመመልከት ለውጪው አለምም በማስተዋወቅ ሃገርን መገንባትና ማበልፀግ አለብን  ውጤታማም  እንሆናለን ብለዋል፡፡

ጨበራ ጩርጩራ፣ ጎርጎራንና ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን  መጎብኘታቸውን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ ያለቁ ፕሮጀክቶች ልዩና ውብ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በወንጪ ደንዲ  አረንጓዴነትና  የቦታው አቀማመጥ እንደተማረኩ ገልፀው በመጎብኘት  አካባቢውንም መደገፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ቦታው  ለአዲስ አበባ ያለው ቅርበት ፣የመንገዱ  ምቹነት  ሰው መጥቶ እንዲጎበኘው ፣ እንዲደሰት ፣እንዲማር  እና ባህሉንም እንዲያውቅ ማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 


 

በጉብኝቱ የህብረተሰቡን ባህል ማወቃቸውንና  በተለይ በኢኮ-ቱሪዝም ገቢ የሚያስገኝና  ለውጪውም አለም  የኢትዮጵያን ውበት የሚያሳይ መሆኑን ነው የተናገሩት ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲዳከም ክፉ የሚያወሩ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው  መሰል ቦታዎችን በማስተዋወቅ  መቀልበስ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ  በኢኮ-ቱሪዝም ያከናወነችውን ስኬት በተግባር ያሳየ  መሆኑን ገልፀው ፕሮጀክቶቹ  የሀገሪቱን  ኢኮኖሚ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የወንጪ ደንዲ ኢኮ-ቱሪዝሙ አካባቢውን  ያነቃቃል፣ ሱቆች፣ ትንንሽ ቢዝነሶች እንዲሳፋፉ እድል ይፈጠራልም ብለዋል፡፡ 

የሁለተኛው ትውልድ አባላት  ወደ ሀገር እየገቡ መሆናቸውን ገልጸው መሰል ቦታዎችን በመጎብኘት  ስለኢትዮጵያ ውበት እና የተፈጥሮ ሃብት እንዲረዱ ጥሪ አቅርበው ወንጪ ደንዲንም  በመጎብኘት ለአለም እንዲያስተዋውቁ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም