በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖሊስ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የቀድሞ አባላቱ ተጨማሪ አቅም ይሆናሉ - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖሊስ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የቀድሞ አባላቱ ተጨማሪ አቅም ይሆናሉ - ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ጥር 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖሊስ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ አባላት ተጨማሪ አቅም ይሆናሉ ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማኅበር ውይይት እያካሄደ ነው።
የማኅበሩ የበላይ ጠባቂ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ ዘመናዊ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የቀድሞ የፖሊስ ሠራዊት አባላት የካበተ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው በመሆኑ በተቋምና በሠራዊት አቅም ግንባታ የላቀ አበርክቶ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሀገራቸውን አገልግለው ጡረታ የወጡ አባላትን ማኅበሩ መሰብሰቡን ተናግረው፤ አባላቱ ያላቸውን ልምድና አቅም አሁን ላሉት የሠራዊት አባላት በማጋራት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሀገሩን እና ሕዝቡን በስነ-ምግባር፣ በጀግንነት እና በሰብዓዊነት የሚያገለግል የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የፌደራል ፖሊስ የጀመረው የሪፎርም ሥራ በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘመናዊ የፖሊስ ሠራዊት ለመገንባት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊት አባላት ማኅበር እንዲጠናከርም አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ አረጋግጠዋል።
ፌደራል ፖሊስ ሕዝባዊነቱን ጠብቆ ሀገርን እና ሕዝብን የማገልገል ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።