የሀላባ የዘመን መለወጫ ''ሴራ'' በዓል የማጠቃለያ መርሃ ግብር በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀላባ የዘመን መለወጫ ''ሴራ'' በዓል የማጠቃለያ መርሃ ግብር በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ሁለገብ ስታዲየም እየተከበረ ነው
ሃላባ፤ ጥር 5/2016(ኢዜአ)፦ የ2016 ዓ.ም የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ''ሴራ'' በዓል ማጠቃለያ መርሃ ግብር በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ሁለገብ ስታዲዮም በደማቅ ሥነ ሥርዓት እየተከበረ ነው።
በከተማዋ የሚኖሩ፣ ከዞኑና ከሌሎችም አካባቢዎች የመጡ የብሔሩ ተወላጆች በአሉን እያከበሩ ያሉት በሀላባ ባህላዊ አልባሳት አሸብርቀው ነው።
በአሁኑ ወቅት በክብረ በዓሉ ላይ የሀላባ ባህላዊ ጭፈራዎች፣ እና መሰል ባህላዊ ትዕይንቶች በደማቅ ስነ ስርዓት እየቀረቡ ሲሆን በዓሉን አስመልክቶ የተዘጋጀ አውደ ርእይም እየተካሄደ ነው።
የ''ሴራ'' በዓል በየአመቱ በታህሳስ ወር ወይም በብሄረሰቡ አጠራር መንገሳ በሚባለው ወር የሚከበር ሲሆን፣ክብረ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ከታህሳስ ወር መጨረሻ እስከ ጥር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ የሚከበር ነው ተብሏል።
በሀላባ ባህል መሰረት ''ሴራ'' ሁለንተናዊ የብሄሩ መገለጫ ሲሆን፣ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ሁሉ ለጋብቻ የደረሱ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ እርቅ የሚፈጸምበት እና በዓሉ መሰል ማህበረሰባዊ የባህል ተግባራት የሚከናወኑበት መሆኑም ተመላክቷል።
እንዲሁም በ''ሴራ'' በዓል ስለ ሰላም፣ አብሮነት፣ መደጋገፍና መተባበር ይሰበካል፣ ለህዝቦች ሰላም የተሰው ጀግኖችም እንደሚታወሱ ከዞኑ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በተለይ ''ሴራ'' ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረዳዳት “ሚሻላ” በሚል ባህላዊ ክዋኔ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአረጋዊያንና አዛውንቶች የሚደገፉበት ድንቅ ባህልን ያካተተ ሥርዓት ነው ተብሏል።
በክብረ-በዓሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ ከፌዴራል፣ ከክልሎችና ከዞን አስተዳደሮች የመጡ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ታድመውታል፡፡