ቀጥታ፡

የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪካዊ እድገት ለመገንዘብ አስችሎናል - የአውደ ርዕዩ ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2016(ኢዜአ)፦የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪካዊ እድገትና ለውጥ የሚያሳይ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአውደ ርዕዩ ጎብኚዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ "ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" በሚል መሪ `ሃሳብ ከትናንት በስቲያ በሳይንስ ሙዚየም መጀመሩ ይታወቃል።

ይህም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ የዲፕሎማሲውን ታሪካዊ እድገትና ለውጥ የሚያሳይ ሁነት መሆኑን ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው የአውደ ርዕዩ ጎብኚዎች የሚናገሩት። 

ከጎብኚዎቹ መካከል፤ አቶ ጥበበ ገብረ ሥላሴ፤ አውድ ርዕዩ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪካዊ እድገት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ በሰራችው ዲፕሎማሲ በርካታ ጭቁን ሕዝቦች ከባርነት ነጻ እንዲወጡ ያደረገችውን ተጋድሎ መገንዘብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

በአውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የደረሰችበትን ደረጃ በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።



 

ወጣት ብሩክ ገብረመድኅን በበኩሉ፤ አውድ ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን ተሰሚነት በግልጽ እንዳውቅ አድርጎኛል ሲል ገልጿል።

መንግሥታት ቢለዋወጡም በአገር ሉዓላዊነት ላይ በፍጹም ድርድር እንደሌለ መረዳቱን ተናግሯል። 

አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ታሪክ ማሳያ መሆኑንና ወጣቶች አውድ ርዕዩን ቢያዩ ትልቅ ግንዛቤ እንደሚያገኙበት ተናግሯል።


 

ሌላኛው ጎብኚ አቶ ግዛቸው ሙሉጌታ ኢትዮጵያ አሁን ላይ እያከናወነችው ያለው ሁሉን አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመገንዘብ መቻሉን ገልጿል።

የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ለዚህም ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን መቆም እንደሚገባው ነው አስተያየቱን የሰጠው። 

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ እስከ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም