ቀጥታ፡

በምድርም በሰማይም አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት በመገንባቱ ከውስጥም ከውጭም የሚነሳ ተጻራሪ አካል ኢትዮጵያ ላይ ፍላጎቱን በኃይል ሊያሳካ አይችልም - ሌተናል ጄኔራል አለምእሸት ደግፌ

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2016(ኢዜአ)፦ በምድርም በሰማይም አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት በመገንባቱ ከውስጥም ከውጭም የሚነሳ ተጻራሪ አካል ኢትዮጵያ ላይ ፍላጎቱን በኃይል ሊያሳካ እንደማይችል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አለምእሸት ደግፌ ተናገሩ።

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለ9ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ከፍተኛ መኮንኖች ዛሬ አስመርቋል። 

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ኮሌጁ የተቋምን ግብ ለማሳካት የሚያግዙ ብቁ የጦር መሪዎችን ለማፍራት እየሠራ ነው። 

በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት ከፍተኛ መኮንኖች በቀጣይ በሚሰጣቸው ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም የሚያስችላቸውን እውቀትና ክህሎት መጨበጣቸውን ጠቁመው ተመራቂ ከፍተኛ መኮንኖች የአገሪቱን ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ ጠንክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ጎን ለጎንም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል አደረጃጀት እንዳለውና የሰራዊቱ አባላትና አመራሮች በአግባቡ እያሰለጠነ መሆኑን ገልጸዋል።

መከላከያ ሠራዊት "በምድርም በሰማይም በአስተማማኝ ልናሰማራቸው የሚችሉና በጠላቶቻችን ላይ ከባድ ውድመት የሚያደርሱ  ዘመናዊ መሳሪያዎችን እየታጠቀ ነው" ሲሉም ተናግረዋል። 

ይህም በውስጥም ሆኖ ከውጭ የሚመጣ ጥቃት ለመመከት እንደሚያስችል አረጋግጠዋል። 


 

የኮሌጁ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች በሥነ-ምግባር፣ በወታደራዊ ስትራቴጂ፣ በወታደራዊ አመራር፣ የጦርነት አመራር ትምህርትና የኅብረት ዘመቻ ዘርፍ በዋነኝነት ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል። 

ሥልጠናው የአገሪቱን ሉዓላዊንትና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ብቁ  ሥልታዊ አመራር ለመስጠት የሚያስችል አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን ተናግረዋል። 

የወሰዱት ወታደራዊ አመራር ሥልጠና ዘመኑ የሚጠይቀው ዕውቀት በመጨበጥ አገርንና ሕዝብን በላቀ ደረጃ ማገልገል እንዲችሉ የሚያዘጋጃቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሰራዊቱን የአገር ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ከፍታ አስጠብቆ ለመሄድ እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በተለይም በተለያዩ ጊዜያት በአውደ ውጊያ የተገኙ ልምዶች በመቀመርና ዓለም የደረሰበትን የወታደራዊ ሳይንስ፣ ጥበብና ቴክኖሎጂ እድገት ጋር የተጣጣመ ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።  

ተመራቂዎች መኮንኖች በበኩላቸው የተሰጣቸው ሥልጠና ባላቸው ልምድ ላይ አቅም የጨመረ በመሆኑ በቀጣይ አገራዊ ተልኳቸውን በብቃት ለመውጣት የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሌተናል ኮሎኔል አንተነህ ከፍአለኝ ሥልጠናው በዋናነት የነበራቸውን ልምድና ክህሎት ለማሳደግ እድል የሰጠ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም በሥልጠናው በተለይም ሥልታዊ አመራሩ አስፈላጊውን የሙያ ክህሎት ማግኘት ችሏል ብለዋል። 

ሥልጠናው በአራት ምዕራፍ ተከፋፍሎ ሲሰጥ መቆየቱን ጠቅሰው የአመራሩን ብቃት ለማዳበር ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን የተናገሩት ደግሞ ሌተናል ኮሎኔል ደረጄ ዳበሳ ናቸው።   


 

በምረቃ መርኃ ግብሩ የሠራዊቱና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። 

በምረቃ ማጠናቀቂያው ኮሌጁ እያከናወናቸው የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታ በተመለከተ የተዘጋጀው  የፎቶ አውደ ርዕይ ተጎብኝቷል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም