ቀጥታ፡

የክልሉ ወጣቶች በሰላም፣ በልማትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተሳትፏቸውን ማጠናከር አለባቸው- ምክር ቤቱ

ቦንጋ ፤ ጥር 4 /2016 (ኢዜአ)፡- የክልሉ ወጣቶች በሰላም፣ በልማትና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው  የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ወጣቶች ምክር ቤት አሳሰበ።

ክልሉ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤት በቦንጋ ከተማ በይፋ መስርቷል።


 

የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤት ሰብሳቢ ወጣት ይስሃቅ ንጉሴ እንዳለው፤ ምክር ቤቱ 13 ሥራ አስፈጻሚና 42 የምክር ቤት አባላት አሉት፤  ከምክር ቤቱ አባላት 50 በመቶ ሴቶች ናቸው።

ምክር ቤቱ የክልሉ ወጣቶች በሰላም፣ በልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑና በአገራዊ ጉዳዮች ሚናቸውን እንዲጫወቱ   አበክሮ እንደሚሰራ ገልጿል። 

የክልሉ ወጣቶች በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ያላቸውን ተሳትፎ  ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስቧል።

ባለድርሻ አካላት ምክር ቤቱን ለማጠናከር ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቋል። 

 የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ በወቅቱ እንደገለጹት፤  ወጣቶች ያላቸውን አቅምና ዕውቀት ተጠቅመው ለአገር ልማትና ብልጽግና የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲወጡ ለማስቻል መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው።


 

 “ወጣቶች ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ለዚህም በመንግሥትና ወጣቶች መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰው፣ ዛሬ ደግሞ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር በመተባበር የክልሉን የወጣቶች ምክር ቤት በይፋ ማቋቋም  እንደተቻለ አብራርተዋል።

“ምክር ቤቱ የተጠናከረና የወጣቶችን መብት በማስከበር ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንዲችል ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት መኩሪያ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ የክልሉ ወጣቶች ድምጻቸውን የሚያሰሙበት፣ ሀሳባቸውን የሚያካፍሉበት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት አደረጃጀት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፤ የክልሉ ወጣቶች ለክልሉ ብሎም ለአገር  ግንባታና ሰላም መከበር የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።


 

ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ውጤታማነት ድጋፍ እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመድረኩ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም