ቀጥታ፡

በበልግ ሁለተኛ ዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ሊያጋጥም ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2016(ኢዜአ)፦ በበልግ ሁለተኛ ዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ  ሊያጋጥም ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አሳሰበ።    

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት በመጪው በልግ 2016 ዓ.ም በሚኖረው የወቅት አየር ትንበያ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።


  

በውይይቱ ላይ የዘንድሮ ክረምት ትንበያና መሬት ላይ ያለው ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን ቀጣይ በልግ የሚኖረው የአየር ጸባይ፣ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችና የባለድርሻ አካላት ሚና ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።   

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በዘንድሮ የበልግ ወቅት በተሰጠው ትንበያ መሰረት የአየሩ ሁኔታ በኤልኒኖ ተጽእኖ ሥር ይቆያል። 

በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች የሱማሌ፣ የቦረና፣ የደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ ዞኖች የባሌ ጉጂ እንዲሁም ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይጠበቃል። 

በሌሎች አካባቢዎችም ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚኖር ትንበያው ማመልከቱን ጠቁመው በጥቅሉ የዘንድሮ በልግ ጥሩ ዝናብ እንደሚገኝበት ትንበያው አመልክቷል ብለዋል። 

በመሆኑም በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑና ሌሎችም መኽር አብቃይ አካባቢዎች ከወዲሁ ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።   

አየር ትንበያው እንደሚያሳየው ድርቅ እንደማያጋጥም ለማወቅ ተችሏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ትንበያውን የግብርና፣ ውኃና የጤና ዘርፎች በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል። 

የመኽር አብቃይ አካባቢዎች በተለይም በበጋ መስኖ የለሙ አካባቢዎች ጥሩ ምርት እንደሚያገኙ ጠቁመው በግድቦች የሚያዘውን ውሃ ማሻሻል፣ ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲኖር አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም አብራርተዋል።

በበልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነባቸው አካባቢዎች አልፎ አልፎ ከሚጠናከረው ዝናብ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ጎርፍ ሊያጋጥም ስለሚችል የሚመለከታቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

የግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት የሚሰጣቸውን ትንበያዎች በግብዓትነት በመጠቀም ውጤታማ የምርት ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።    

የዘንድሮ በልግም በተሰጠው ትንበያ መሰረት ምርት ሂደቱን ለመምራት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም