ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2016(ኢዜአ) ፦ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
በበርካታ ክልሎች ሲካሄድ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታ በመጪው ሳምንት በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክሩ ሂደቶች ለማከናወን ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
ነፍጥ ያነሱ ወገኖች በሰላማዊ መንገድ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ መንግስት ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ ሰጥቶ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ የበለጠ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ቀደም ብሎ የምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ በሩቅ ሆነው ቅሬታ ሲያነሱ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደነበሩ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ግን የኮሚሽኑን ትክክለኛ ተልዕኮ በቅርበት በመረዳት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክር ስኬት በጋራ ለመስራት መግባባት ስለመፍጠራቸው አንስተዋል።
ለአብነትም በቅርቡ ከአፋር ህዝቦች ፓርቲ፣ ከሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲና ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ማዕቀፍ መፈረሙን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ እንደ ገለልተኛ ተቋም ከሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት እንደሚፈልግ ገልጸው፣ ሁሉም ፓርቲዎች ወደ ምክክር እንዲገቡ መንግስት የበለጠ ማገዝ እንዳለበት አንስተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮሚሽኑ በሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የተሳታፊ ልየታ ማካሄዱን አስታውሰዋል።
በመጭው ሳምንት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተሳታፊዎች ልየታ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አክለውም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክር ሂደት የሚሳተፉበት ዕድል መመቻቸቱን ገልጸዋል።
በዚህም እስካሁን በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በፓሲፊክ እና እስያ እንዲሁም በአውሮፓ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በበይነ መረብ ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።
ከሰሞኑም በአሜሪካ ከሚኖሩ ዳያስፖራ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይቱ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።