ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ 5 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ 5 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታወቀ
ጎንደር፤ ጥር 4/2016 (ኢዜአ)፡- ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ5 ሺህ አዲስና ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስማማው ዘገዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ለመቀበል የሚያስችሉ አብይና ንኡሳን ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ዝግጅት አድርጓል፡፡
በዚህም በመጀመሪያው ዙር አንድ ሺህ 500 ነባር ተማሪዎችን ጥር 15 እና 16 ቀን 2016 ዓ.ም መቀበል የሚያስችለውን ጥሪ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
በጥር ወር መጨረሻ ደግሞ 3 ሺህ 500 አዲስና የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጣቸውን ተማሪዎች ለመቀበል በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የተማሪዎችን የምግብ አቅርቦትም ለቀጣይ ስድስት ወራት ፍጆታ የሚውሉ የግብርና ምርቶችን ከአቅራቢ ድርጅቶች በበቂ መጠን ግዢ በመፈጸም ማሟላት ተችሏል ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ግብዕት የሆኑ ስኳርና የምግብ ዘይት ግዢ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ የምግብ አዳራሾችንና የምግብ ማብሰያ ስፍራዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የተማሪዎች የመኝታና የመማሪያ ክፍሎች እድሳት ስራ መጠናቀቁ አመልክተው፤ ቤተ መጻህፍቶች ቤተ-ሙከራዎችና የኮምፒውተር ማእከላትም በግብዓት እንዲሟሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መምህራን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የትምህርት ፕሮግራሞችን ጀምረው ማጠናቀቅ እንዲችሉ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው፤ የማስተማሪያ "ሞጅሎች" በበቂ ሁኔታ መሟላታቸውን አስረድተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የተመደቡ አዲስና ነባር ተማሪዎች በተመቻቸ ሁኔታ ወደ ትምህርት ገበታ መምጣት እንዲችሉ ከጎንደር ከተማ ወደ ደባርቅ ከተማ ነጻ የትራንሰፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶች መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የሚገኝ ሲሆን በ2008 ዓ.ም ማስተማር መጀመሩም ተመልክቷል።