ቀጥታ፡

በዞኑ ዘላቂ ሰላም ለማስፋን በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ድጋፉን የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል 

መተማ ፤ ጥር 04/2016(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ እያደረገ ያለውን እገዛና ድጋፍ የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የምዕራብ ጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት አስተባባሪና የ504ኛ ኮር አዛዥ ገለጹ።

በገንዳ ውኃ ከተማ በወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ዙሪያ ከፀጥታ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።

የምዕራብ ጎንደር ቀጣና ኮማንድ ፖስት አስተባባሪና የ504ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መካሽ ጀንበሬ እንዳሉት፤ ሠራዊቱ የቀጣናውን ሰላም ለማስጠበቅና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።

ሠራዊቱ ይህን ተግባሩን ሲያከናውን የአካባቢው የፀጥታ ኃይል ከመከላከያ ጎን በመሆን እያደረገ ላለው እገዛ አመስግነዋል።

በአካባቢው ሰላምና ደህንነት እንዳይኖር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የሚከተሉት መንገድ የጥፋት መሆኑን በመረዳት ወደ ሰላማዊ መንገድ ሊመጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአካባቢው ህዝብ ለፀጥታ ስራ እያደረገ ያለውን እገዛ የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ቢክስ ወርቄ በበኩላቸው፤ የዞኑን ሰላም አስጠብቆ ለመዝለቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዝቡን አንድነት ለማዳከምና ለመሸርሸር የሚጥሩ ቡድኖች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ወደ ሰላም እንዲገቡና የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ባለፉት ጊዜያት በተሰራ የህግ ማስከበር ስራ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ሁሉም ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል። 

የከተማዋ የሚሊሻ አባል አቶ አማረ ሻምበል በበኩላቸው፤ አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም በማምጣት የልማት ስራዎች ዳር እንዲደርሱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ በየደረጃው ያሉ የአካባቢው የኮማንድ ፖስት አባላትና የፀጥታ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም