ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባህር በር ስምምነት ማዕቀፍ የማሪታይም ተልዕኮን ይበልጥ ለማቀላጠፍ ዕድል የሚፈጥር ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባህር በር ስምምነት ማዕቀፍ የማሪታይም ተልዕኮን ይበልጥ ለማቀላጠፍ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ገለፀ።  

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አብዱልበር ሸምሱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የገቢና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ የተሰማሩ መርከቦች የባህር በር ባለመኖሩ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና ይስተዋላል።

የኢትዮጵያ የጭነት መጠን በአጭር ጊዜ ከእጥፍ በላይ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ገልፀው፤ ለአብነትም ወደ ሀገር ውስጥ ብቻ በዓመት 20 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ገቢ ዕቃ እንደሚጓጓዝ ገልፀዋል።


 

በዚህም ኢኮኖሚውን ለመሸከም የሚችል እና ከጊዜ እና ከዋጋ አኳያ ጥራት ያለው ሎጂስቲክስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አማራጭ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

አማራጭ የባህር በር የገቢና ወጪ ንግድ ከፍተኛ ወጪን ከመቀነስ ባሻገር "በብሉ ኢኮኖሚ" የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ አንስተዋል።

በወጪ ንግድ ረገድም በተለይም በፍጥነት የሚበላሹ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የገለጹት።

በቅርቡ በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተደረሰው የባህር በር ስምምነት ማዕቀፍ የወደብ ንግድን በማሳለጥ በወጪና ገቢ ንግድ መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልፀዋል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት ሲሰሩ የነበሩ ተግባራትን ይበልጥ ለማጎልበት እና የባለሥልጣኑን ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያስችለው ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም