ዓመታዊ የሚሲዮን መሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ዓመታዊ የሚሲዮን መሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ጥር 4/2016(ኢዜአ)፦ዓመታዊው የሚሲዮን መሪዎች ስብስባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ስብስባውን ከፍተዋል።
የስብስባውን መክፈቻ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ገለጻ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም (ዶ/ር)፤ አቶ ደመቀ በ2016 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተከናወኑ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራዎች የተመለከተ ሪፖርት ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚገኙ የተለያዩ የሥራ ዘርፎችም ሪፖርታቸውን አቅርበው ውይይት እንደሚደረግበት አመልክተዋል።
በሩብ ዓመቱ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው በተለይም በባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስክ ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኗን ጠቅሰው የብሪክስ አባል መሆኗን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ በኩል የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ የውጭ አገራት ጉብኝቶች እንዲሁም የሌሎች አገራት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ትብብርን ከማጠናከር አኳያ የራሱ አብርክቶ አለው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ አገራት ጋር ያደረገቻቸው የጋራ ኮሚሽን ስብስባዎችም ለሁለትዮሽ ትብብር መጎልበት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት አምባሳደር መለስ።
በሌላ በኩል ብሩንዲ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (Cooperative Framework Agreement) በፓርላማዋ ማጽደቋ እንደ ስኬት እንደሚወሰድና ቀጣናዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።
ከስብስባው ጎን ለጎን አምባሳደሮቹ የመስክ ጉብኝት እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።
ስብሰባው እስከ ጥር 18/2016 ዓ.ም ይቆያል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት አካል በሆነው በዚሁ ስብሰባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።