ቀጥታ፡

አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በክልሉ ፈጣንና ዘላቂ ዕድገት እንዲመዘገብ መሰረት የሚጥል ነው

ሆሳዕና ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፡- አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በክልሉ ፈጣንና ዘላቂ ዕድገት እንዲመዘገብ መሰረት የሚጥል በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈፃሚ እንዲሆን እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ ።

አዲሱን የኢንዱስትሪ ፖሊሲና ተኪ ምርት ስትራቴጂን ወጥ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግን ያለመ የምክክር መድረክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በክልሉ ፈጣንና ዘላቂ ዕድገት እንዲመዘገብ መሰረት የሚጥል መሆኑን በመድረኩ ተናግረዋል።

በክልሉ ዘርፉን መምራትና ተግባራዊ ማድረግ የሚችል የሰው ሀይል መኖሩን ጠቅሰው ፖሊሲውን በአጭር ጊዜ ተፈጻሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ለዚህም ስኬታማነት የዘርፉን ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላትን የማብቃት ስራ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ዘርፉ ለክልሉ የኢኮኖሚ እድገት መሆኑን ጠቁመው አዲሱ ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የሚገጥሙ ተግዳሮቶች እንዳይኖሩ ምቹ ከባቢን መፍጠር ላይ ይሰራል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የምርት መጠን፣ አይነትና ጥራትን ማሳደግ፣ የስራ እድል እንዲፈጥር ማድረግ፣ የትኩረት መስኮችን መለየት፣ ምርትና ምርታማነትን ማጎልበት ላይ ሊሰራ ይገባል ተብሏል።

በዚህም ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻል፣ የኤክስፖርት ምርቶችን ማስፋት፣ ዘርፉን በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረግና የእሴት ሰንሰለቱን ማጠናከርም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተነስቷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ በተለያየ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ተነሳሽነት በመጨመር በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው እንዲሰሩ ያስችላል ብለዋል።


 

ለፖሊሲ ትግበራው አስቻይ የሆኑ አሰራሮችን ለመተግበር በክልሉ ያሉ ሀብቶችን በመለየት ለዘርፉ ስኬት የክልሉ መንግስት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት የግል ባለሀብቱን በማሳተፍ በኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠር በማድረግ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣም አስገንዝበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለፁት፤ በክልሉ ያለውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም  አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊስ የሚያበረክተዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።


 

በዚህም አርሶ አደሩን በማደራጀት ያፈራውን ሀብት ወደ ኢንዱስትሪ እንዲያቀርብ በማድረግ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።

ተኪ ምርቶችን መጠቀም ሀገሪቱ ምርቱን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የምታወጣውን ወጪ በማስቀረት ረገድ በጎ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር የተናገሩት የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ  ጁሃር ናቸው።


 

ቢሮዉ በመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ ምርቶችን ገዝቶ በመጠቀም መደገፍ ስለመጀመሩ ጠቅሰው ተግባሩን አጠናክሮ በማስቀጠል ለዘርፉ ስኬት እንደሚሰራም ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ካቢኔ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም