ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ ሁሉን አቀፍ የትብብርና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ትክክለኛና ወቅታዊ ነው - ሶፌፓ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ ሁሉን አቀፍ የትብብርና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ትክክለኛና ወቅታዊ ነው - ሶፌፓ
ጂግጂጋ፤ ጥር 03/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ሁሉን አቀፍ የትብብርና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ትክክለኛና ወቅታዊ መሆኑን የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀ መንበር ዩሱፍ ሁሴን ገለጹ።
የሶማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ (ሶፌፓ) ሊቀ መንበር የሱፍ ሁሴን በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር ሰጥቶ መቀበልን ባስቀደመ የዲፕሎማሲ ሂደት የባህር በርና ወደብ ለማግኘት የሚያስችላትን መንገድ የከፈተ ሁሉን አቀፍ የትብብርና የአጋርነት መግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ትክክለኛና ወቅታዊ ነው።
የመግባቢያ ስምምነቱ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ለመመለስ እድል የሚከፍት የዲፕሎማሲ ስኬት ስለመሆኑ የፓርቲው ሊቀ መንበር ተናግረዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ገቢራዊ ሲደረግ ለአገር የሚኖረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ በተጨማሪ በቀጣናው የመሰረተ ልማትና ተቋማት ግንባታ በማስፋፋት የተጠናከረ ህጋዊ የንግድ ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችልም አቶ የሱፍ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ያለምንም የባህር በር ለዘመናት እንዲኖር መፍቀድ የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ችግር ሊፈታ የሚችለውን የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን መደገፍ እንደሚገባ ነው ሊቀ መንበሩ የገለፁት።
ኢትዮጵያ የባህር በር አልባና የምጣኔ ሀብት ጥገኛ ሆና እንድትቀጥል በመፈለግ ከተለያዩ የአገሪቷ ታሪካዊ ጠላቶች ለሚነሱ የፈጠራ ክሶች መንበርከክ እንደማይገባም ገልጸዋል።