የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማጠናከር ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በቅንጅት መስራት ይገባል-ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማጠናከር ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በቅንጅት መስራት ይገባል-ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማጠናከር ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
በዛሬው እለት በአቪዬሽን ዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ተፈርሟል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እና የኢትዮጵያ ኤሮ ክለብ መስራች አቶ ዮናታን መንክር ናቸው።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ያላትን የመልማት አቅም ወደ ተግባር ለመለወጥ በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው።
በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪነትን ለማሳደግና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ይገባል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ሙያተኛን ለማፍራት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ሚኒስቴሩም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፥ የአቪዬሽን ዘርፍ ማደግ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል።
አየር መንገዱ የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሳደግ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በአቪዬሽን ዘርፉ ላይ ከ80 ዓመታት በላይ በተለያዩ የሙያ መስኮች ብቁ የሆኑ ሙያተኞችን የማፍራት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
እስካሁን ድረስ በመስኩ ላይ 1 ሺህ 802 ፓይለቶች በማሰልጠን ማብቃቱን በመግለጽ ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 400 የሚሆኑት በአሁኑ ሰዓት አየር መንገዱን እያገለገሉ እንደሚኙ ተናግረዋል።
የሀገሪቱን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ለማፋጠን በዘርፉ ላይ የሰለጠነ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት ላይ የጀመርናቸውን ስራዎች ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር አጠናክረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።
ዛሬ የተደረገው ስምምነት በአቪዬሽን ኢንደስትሪ ብቁ ሙያተኞችን በሚፈለገው መጠን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ፥ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ እድገትን ያገናዘበ የሰው ሃይል የማሟላት ተቋማዊ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።
ባለስልጣኑ ኢንዱስትሪው ከሰው ሀይል ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን ማነቆዎች ለመፍታት የዘርፉን የቀጣይ 15 ዓመታት የሰው ሃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እቅድ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።