ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና አህጉር ደረጃ የነበራትን ገናና የዲፕሎማሲ ታሪክ በሚገባ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና አህጉር ደረጃ የነበራትን ገናና የዲፕሎማሲ ታሪክ በሚገባ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍና አህጉረ ደረጃ የነበራትን ገናና የዲፕሎማሲ ታሪክ በሚገባ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተገለጸ።
ትላንት የተከፈተው የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደርዕይ አካል የሆነ የፓናል ውይይት ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያውያን በታሪክ ነጻነታቸውን አስከብረው ለመኖር፣ በትምህርትና በሳይንስ እድገት ለማሳየት፣ ከሌሎች አገሮች ጋር ግንኙነትና ትብብር ለማሳደግ ካላቸው መሻት የተነሳ የዲፕሎማሲ ጉዞን ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በየዘመኑ ወሳኝ ቦታ ይዞ ኖሯል ያሉት አቶ ደመቀ፥ በመንግስታት ቅብብሎሽ ተጠብቆ የዘለቀውን የዲፕሎማሲ ከፍታ በጽናት ማስቀጠል ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ዛሬ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ታሪክ የሚዳስሱ ጽሑፎችና ተሞክሮዎች በምሁራንና አንጋፋ ዲፕሎማቶች ቀርበዋል።
የታሪክ ምሁሩ ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ላይ ትኩረት ባደረገው ገለጻቸው፥ ሀገሪቱ በመካከለኛው ዘመን ግንኙነትን ለመፍጠር ብዙ እርምጃዎችን መውሰዷን ጠቅሰዋል።
በተለይ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ሀገርን ወደዘመናዊነት ለማሻገር ከውጭ መንግስታት ጋር ትብብሮች ስለመጀመራቸውም ገልጸዋል።
ፕሮፌሰር ባህሩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ጥረቷ የፓን አፍካኒዝም ንቅናቄን በመጀመር አህጉራዊ ተቋማት እንዲመሰረቱ እንዲሁም ለጎረቤቶቿ ሰላም ጉልህ ሚና መጫወቷን ጠቅሰዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፥ በቀዝቃዛው ጦርነትና ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ዋና ዋና ስኬቶችን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬትና ውጣውረድ የታጀበ የነጻነት ታሪክ ያላት አገር መሆኗን የጠቀሱት አምባሳደር ዲና የውጭ ግንኙነት ስራዎቿ ከጥንት ጀምሮ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረጉ ናቸው ብለዋል።
የራስን ጥቅም ከማስጠበቅም ባለፈ በዓለም ሰላም ጥበቃ፣ ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ነጻነት መጎናጸፍ ጉልህ ዲፕሎማሲያዊ ገድል መፈጸሟንም ተናግረዋል።
ይህንን ገናና የዲፕሎማሲ ታሪክ በሚገባ ለዓለም ከማስተዋወቅ አንጻር ክፍተቶች እንዳሉ የጠቀሱት አምባሳደሩ፥ በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
አንጓፋዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ቆንጅት ስነጊዮርጊስ በዲፕሎማትነት ባገለገሉባቸው ዘመናት ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ የነበራትን የዲፕሎማሲ ስኬቶችና ፈተናዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም መንግስታት ማህበር (የተባበሩት መንግስታት) አባል፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ህብረት) መስራች ከመሆን ጀምሮ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች ትልቅ ስፍራ ነበራት ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፥ የዲፕሎማሲ ስራ የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ኃይልን በሁሉም አማራጮች የማጠናከር ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት በአግባቡ የሚያስከብር ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ አካሄድን መከተል ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች የወከሉ አምባሳደሮች፣ አንጋፋ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና ሌሎች በፓናል ውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።