ለ108 የውጪ ሀገር ጋዜጠኞችና የፊልም ባለሙያዎች የአጭር ጊዜ የቀረፃ ፈቃድ ተሰጥቷል- የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ባለፉት ስድስት ወራት ለ108 የውጪ ሀገር ጋዜጠኞችና የፊልም ባለሙያዎች የአጭር ጊዜ የቀረፃ ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ህብረተሰቡ በማንኛውም ሁኔታ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን እንዲከላከልም ጥሪ አቅርቧል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ31 የውጪ ሀገር መገናኛ ብዙኃን፣ ከፊልም ሰሪ ድርጅቶችና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ለመጡ ለ108 ጋዜጠኞችና የፊልም ባለሙያዎች የአጭር ጊዜ የቀረፃ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

ፈቃዱ የተሰጠው በታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች እንዲሁም ባህላዊ እሴቶች ዙሪያ ዶክመንተሪ ፊልም ለመስራት፣ ከመንግስት ኃላፊዎችና ከታዋቂ አትሌቶች ጋር ቃለ-መጠይቅ ለማድረግ መሆኑም ተገልጿል።

በተጨማሪም ወቅታዊ ጉዳዮች እና የልማት ስራዎችን በሚመለከት የዜና ዘገባ ለመስራት ፈቃድ ለጠየቁ ለ31 የውጪ ሀገር መገናኛ ብዙኃንና ድርጅቶች አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸውን ገምግሞ የአጭር ጊዜ የቀረፃ ፈቃድ መስጠቱን ባለስልጣኑ ገልጿል።

ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን፣ ባህላዊ እሴቶችን፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎችን በዘገባና በዶክመንተሪ ፊልሞች ለዓለም ለማስተዋወቅ ለሚመጡ ጋዜጠኞችና የፊልም ባለሙያዎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባባር በተለያዩ ቦታዎች ተንቀሳቅስው እንዲሰሩ ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።

በቀጣይም ባለሥልጣኑ የጥምቀት በዓል እና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔን ለመዘገብ ለሚመጡ የውጪ ሀገር ጋዜጠኞች እና የፊልም ባለሙያዎች አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።

ህብረተሰቡ በማንኛውም ሁኔታ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሲመለከት በ9192 ነፃ የስልክ መስመር ደውሎ እንዲያሳውቅ ጥሪ ማስተላለፉን ከባለስልጣኑ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም