ከዚህ በኋላ ግብርና የሚሸሹት ሳይሆን ጠንክረው በመስራት ለአገር የሚተርፉበት ነው - ሚሊየነሩ አርሶ አደር አቶ አሸናፊ አያሌው - ኢዜአ አማርኛ
ከዚህ በኋላ ግብርና የሚሸሹት ሳይሆን ጠንክረው በመስራት ለአገር የሚተርፉበት ነው - ሚሊየነሩ አርሶ አደር አቶ አሸናፊ አያሌው
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016(ኢዜአ)፦ ከዚህ በኋላ ግብርና የሚሸሹት ሳይሆን ጠንክረው በመስራት ለአገር የሚተርፉበት ወሳኝ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው ሲሉ ሚሊየነሩ አርሶ አደር አቶ አሸናፊ አያሌው ተናገሩ።
በምስራቅ ሸዋ ዞን በግብርና ስራ የሚተዳደሩት አቶ አሸናፊ አያሌው በ5 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የግብርና ስራ ጀምረው ዛሬ ሚሊየነር መሆናቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር አሸናፊ በሞጆ አካባቢ ሽራ ዲባንዲባ ቀበሌ በ110 ሚሊዮን ብር ያስገነቡት ሆቴልና ሪዞርት ሊመረቅ ነው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አርሶ አደሩ ቀደም ባለው ጊዜ በአራት ሄክታር ማሳቸው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ጤፍና ስንዴ ሲያመርቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም ለዓመታት ባካሄዱት ግብርና ብዙም ሳይለወጡ በውጣ ውረድ ውስጥ ለማለፍ መገደዳቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ግን በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴና በመስኖ ልማት በመታገዝ በዓመት ሶስት ጊዜ እንደ ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ በማምረት በአጭር ጊዜ መለወጣቸውን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ እንደ አቮካዶ ያሉ ቋሚ ተክሎችን በማልማት ከፍተኛ የሆነ ገቢ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
ከእሳቸው ማሳ ተሰብስቦ ወደ ወጪ ከተላከ የአቮካዶ ምርት 250 ሺህ ዶላር የውጪ ምንዛሪ መገኘቱንም ነው የተናገሩት።
መንግስት ለግብርናው የሰጠው ትኩረትና ለአርሶ አደሩ የሚያደርገው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ ድጋፍ ላይ የአርሶ አደሩ ጥረት ከታከለበት ከራስ አልፎ ለማህበረሰብና ለአገር መጥቀም የሚችል ስራ መስራት ይቻላል ብለዋል።
ግብርናን አጥብቀው ከያዙት ከራስ አልፎ ለሌሎች የሚበቃ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ከዚህ በኋላ ግብርና የሚሸሹት ሳሆን ጠንክረው በመስራት ለአገር የሚተርፉበት ነው ብለዋል።
በዚህ ወቅት አጠቃላይ ካፒታላቸው ወደ አንድ ቢሊየን መጠጋቱን ገልፀው በ110 ሚሊየን ብር ሆቴልና ሪዞርት መገንባታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የቄራ ድርጅትና መጋዘን ያላቸው ሲሆን 206 አርሶ አደሮችን አየደገፉ መሆኑን አንስተዋል።
ዛሬ ላይ በግብርና ዘርፍ በተሰሩ ውጤታማ ስራዎች የተነሳ ብዙ ሰው እኔም ገበሬ በሆንኩ የሚልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
በትጋት መስራትና ቁጠባን ባህል ማድረግ ከተቻለ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል የራሳቸውን የህይወት ተሞክሮ በማንሳት አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አርሶ አደር ግብርና ላይ መበርታት እንዳለበት የመከሩት አርሶ አደሩ መንግሥትም ለግብርናው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።