ወጣት ምሁራን የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሕብረ ብሔራዊነትን የተላበሰ እንዲሆን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣት ምሁራን የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሕብረ ብሔራዊነትን የተላበሰ እንዲሆን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፦ወጣት ምሁራን የአገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ ሕብረ ብሔራዊነትን የተላበሰና የወል ትርክትን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ስራዎች በመደገፍ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
በብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ዋና ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት “የወጣት ምሁራን ሚና ለሀገረ መንግስት ግንባታ” በሚል ሀሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለፁት ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ቢኖራትም የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ ብዙ ስራ ይጠይቃል ።
መንግስት ለአገረ መንግስት የግንባታ ሂደት የሚረዱ ውይይቶችን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሂደቱ የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም በተለይ የወጣት ምሁራን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ሀሳቦችን በማቅረብ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።
በተለይም የጥናትና ምርምር ስራዎቹ አገራዊ፣ አሰባሳቢ እና የወል ትርክቶች ላይ ያተኮሩ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር አቶ መለሰ አለሙ ወጣት ምሁራን በሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ውስጥ ያላቸው ሚና የጎላ ነው ብለዋል።
ወጣት ምሁራን በአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ዙሪያ ባሉ ዕድሎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ የምርምር ስራዎችን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፈሰር ምህረቱ ሻንቆ በበኩላቸው ወጣት ምሁራን የአንድን ሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ አመልክተዋል።
ወጣት ምሁራን ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለአገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ጠይቀዋል።
የኢትዮ-ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ የአገረ መንግስት ግንባታው ሂደት ሕብረ-ብሔራዊ መልክ እንዲኖረው ወጣት ምሁራን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል።
ምሁራኑ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት መንግስት ሂደቱን ለማሳካት ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በማሳሰብ እነሱም የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር ተስፋዬ ጂማ መምህራን ትውልድን ከማስተማር ባሻገር ህብረ ብሄራዊነትን የሚያጸኑ በጥናት የተደገፉ ስራዎችን መስራት አለብን ብለዋል።
የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እንዳልካቸው አሸናፊ በበኩሉ ሁላችንም ታሪክ የምንማር፣ ዛሬን በአግባቡ የምንኖር፣ ነገን የምንመለከት ለትውልድም መልካም ነገር የምናሻግር እንድንሆን የየድርሻችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ብሏል።