የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎች የሚሰጠውን የማህበራዊ አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎች የሚሰጠውን የማህበራዊ አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 3 /2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎች የሚሰጠውን የማህበራዊ አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችለውን ስርዓት ሊዘረጋ መሆኑን ገለጸ።
ለዚህም ሚኒስቴሩ ከዓለም አቀፉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና ከብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ የሶፍትዌር ዝርጋታ፣ የቴክኒል ድጋፍ እና የአቅም ግንባታን ያካተተ መሆኑንና ለዜጎች የሚሰጠውን የማህበራዊ አገልገሎት ዲጂታል በማድረግ ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥ እንዲኖር ለማስቻል ነው።
ስርዓቱ ሲዘረጋ ከብሄራዊ መታወቂያ ጋር እንዲተሳሰር የሚደረግ ሲሆን በማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ የሚያጋጥም ድግግሞሽን በማስቀረት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተመላክቷል።
ዲጂታል እና አካታች የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓቶችን በመዘርጋት እና በመተግበር ከመንግስት ወደ ተጠቃሚዎች የሚደረጉ ክፍያዎችን/ድጋፎችን ለማሳለጥ እና መረጃን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት የቁጥጥርና ክትትል ስራዎችን ለማጠናከር አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሏል፡፡
ስርዓቱ ሁሉንም አይነት የማህበራዊ ጥበቃ አገልግሎቶችን በተለያዩ አማራጮች ተደራሽ ለማድረግ፣ ዘላቂ፣ ወጪ እና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሁም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች አካታች የሆነ ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።