በአቪዬሽን ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
በአቪዬሽን ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፡- በአቪዬሽን ዘርፍ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል የአጋርነት ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኤሮ ክለብ ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት፥ የአቪዬሽን ዘርፍ ማደግ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል።
አየር መንገዱ የአቪዬሽን ዘርፉን ለማሳደግ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸው፥ የዛሬው ስምምነት በዘርፉ ብቁ ሙያተኞችን በሚፈለገው መጠን ለማፍራት ያስችላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ፥ ስምምነቱ የአቪዬሽን ዘርፉን ወደ ላቀ እድገት ለማሸጋገር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ያለትን የመልማት አቅም ወደ ተግባር ልምለወጥ በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የአቪዬሽብን ኢንዱስትሪውን በሚገባው ልክ አልተጠቀንበትም ያሉት ሚኒስትሯ፥ ለዚህም ለዘርፉ ብቁ የሆነ በቂ የሰው ኃይል አለመኖር አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል።
ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ዛሬ የተፈረመውን ስምምነት በአግባቡ እንደሚተገብር እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።