ከተሞችን ለስራና የኑሮ ምቹ ለማድረግ በገቢ አሰባሰብና በካዳስተር ስራዎች ላይ የተጀመሩ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞችን ለስራና የኑሮ ምቹ ለማድረግ በገቢ አሰባሰብና በካዳስተር ስራዎች ላይ የተጀመሩ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል
ድሬደዋ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፦ ከተሞችን ለስራና የኑሮ ምቹ ለማድረግ በገቢ አሰባሰብና በካዳስተር ስራዎች ላይ የተጀመሩ ተግባራትን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በከተማና መሠረት ልማት ሚኒስቴር፣ የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፅሀፈት ቤት ከኢትዮጵያ ከተሞች ትብብር መድረክ ጋር በመተባበር ድሬደዋ ላይ ያዘጋጀው የልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት መድረክ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እንዳስታወቁት ፤ ከተሞቻችንን ምቹ የመኖሪያና የስራ ማዕከላት ለማድረግ በተሠሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጦች እየመጡ ነው።
የአገራችን ከተሞች የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እና ተስፋ ማሳኪያ መሆናቸውን ገልፀው በተለይ በከተማ ካዳስተር ስርአትን እውን በማድረግ የህዝብ ጥያቄዎች በፍጥነትና በቅልጥፍና እየተመለሰ ያለበትን ሂደት ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስማርት ከተሞችን ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ በማሳካትና የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢን እስከ መጨረሻው ድረስ አሠራር ዘርግተው ከሚሰበስቡ ከተሞች ልምድ በመቀመር የተሻለ ለውጥ ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሃርቢ ቡህ በበኩላቸው የአገራችን ከተሞች ከኋላቀር መሠረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ተላቀው በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሠራር ዘርግተው የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ከተሞች የሁለንተናዊ ማዕከል እንዲሆኑ ከማድረግ በዘለለ ለነዋሪዎች ተጨባጭ ምላሽ በመስጠት አበረታች ስኬቶች እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ከተሞች የአገራችንን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ከተሞች የጀመሩትን የተሻለ ዕድገት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ጤናው መድረኩ ከተመሠረተ ከ12 አመታት ወዲህ የከተሞች ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት አስገኝተዋል ።
በተለይ በየደረጃው ለሚገኙ ዜጎች ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ጥራታቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ከ85 በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞችን በአባልነት የያዘ ማህበር ነው።