የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካውያን ዘንድ የይቻላል መንፈስን በማስረፅ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ገንቢ ሚና እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካውያን ዘንድ የይቻላል መንፈስን በማስረፅ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ገንቢ ሚና እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በማስተዋወቅና በአፍሪካውያን ዘንድ የይቻላል መንፈስ በማስረፅ ለሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 78 ዓመታት ኢትዮጵያን ከቀሪው የአፍሪካ እና የዓለም ሀገራት ጋር አስተሳስሯል፡፡
በ135 ዓለም አቀፍ ከተሞች መዳረሻ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኢትዮጵያን ገጽታ በማስተዋወቅና ብሔራዊ ጥቅሟን በማስጠበቅ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ምስረታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላት ሁሉ አየር መንገዱም መሪዎችን በማጓጓዝ ሚናው የጎላ ነበር፡፡
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመፍጠርና በሀገሮች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር በማድረግ የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ ለዓለም ማሳየት የቻለ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና የዲፕሎማሲ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
አየር መንገዱ ለአፍሪካውያን የይቻላል መንፈስን ያወረሰ የአፍሪካውያን ኩራት እንደሆነም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለው ጠቁመዋል።
በዚህም ማህበራዊ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗን ለዓለም ያሳየ ተቋም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊና የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲ በማሳደግ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ተፈሪ መለስ፤ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ከመንግስታቱ ማህበር 'ሊግ ኦፍ ኔሽን' ጀምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን ገፅታ በማስተዋወቅና ዲፕሎማሲዋን በማሳደግ የነበረው አበርክቶ የጎላ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ባልተላቀቁበት ዘመን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ከተሞች በረራ ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡