የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት 385 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት 385 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን አጸደቀ
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፡- የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት በስድስት ዘርፎች 385 የኢትዮጵያ ደረጃዎችን ማጽደቁን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የብሔራዊ ደረጃዎች ምክር ቤት ታኅሣሥ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 38ኛው መደበኛ ስብሰባው በ24 የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የቀረቡ 385 ደረጃዎችን መርምሮ ማጽደቁ ተገልጿል።
የጸደቁት ደረጃዎች በኤሌክትሮ ሜካኒካል፣ በጨርቃ ጨርቅና ቆዳ፣ በአካባቢ ጤናና ደኅንነት፣ በግንባታና በሲቪል ምህንድስና፣ በኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች እንዲሁም ግብርናና ምግብ መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ ጠቅሷል።
ከጸደቁት 385 ደረጃዎች 12ቱ አስገዳጅ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የፈቃደኝነት ደረጃዎች ናቸው።
ከጸደቁት ብሔራዊ የኢትዮጵያ ደረጃዎች 233ቱ አዲስ ሲሆኑ 152ቱ ደግሞ የተከለሱ ደረጃዎች መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ አመልክቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት በቀለ እንደገለጹት በአስገዳጅነትና በፈቃደኝነት የጸደቁት ደረጃዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ የማስተዋወቅና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጀምረዋል።
ጎን ለጎንም “ብሔራዊ የበለጸገ ምግብ ምልክት”ን ይፋ መደረጉን ጠቁመው አምራቾች ብሔራዊ የበለጸገ ምርት ምልክትን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸውና ኅብረተሰቡም ምልክቱ መለጠፉን አይቶ እንዲጠቀም አስገንዝበዋል።
የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ኃብቴ በበኩላቸው አስገዳጅ ሆነው የጸደቁት ደረጃዎች የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችና ኃይል አስተላላፊዎች፣ መድሃኒቶች፣ የሕክምና መሣሪያዎች ይገኙበታል ብለዋል።
አምራቾችና አስመጪዎችም ደረጃዎቹን በመጠቀም ለሀገር ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።