በኢትዮጵያ በሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ብሔራዊ የጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም ሊተገበር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በሚገኙ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ብሔራዊ የጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም ሊተገበር ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፡- በቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ብሔራዊ የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም በቅርቡ እንደሚተገበር የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።
ሚኒስትሯ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ በቱሪዝም ዘርፍ የአገልግሎት ጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት አንስተዋል።
ጎብኝዎችን በሚያስተናግዱ እንደ ሆቴልና መሰል ተቋማት ጥራት እንዳይኖር ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል አለመገንባት፣ የስልጠና እና የልህቀት ተቋማት ማነስን ለማሳያ ጠቅሰዋል።
ችግሩን ለመፍታትም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያ የማድረግ እና ደረጃውን የጠበቀ ወጥ አሰራር የመፍጠር እና የልህቀት ማዕከል ለመገንባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አስጎብኚ ድርጅቶችን ጨምሮ ለቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የብቃት ማረጋገጥ ስራ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ባለኮከብ ሆቴሎች የሚሰጡት የአገልግሎት ጥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ አቻ ሆቴሎች ተመሳሳይ መሆን እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የአገልግሎት ጥራትን በሁሉም አካባቢ ወጥነት ባለው መልኩ ለማሻሻልም ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ብሔራዊ የአገልግሎት ጥራት ማረጋገጥ ፕሮግራም በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ይህም የአገልግሎት ጥራትን ከማስጠበቅ ባሻገር የጥራት መጓደልን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም ኢትዮጵያ ከ40 ዓመታት በኋላ በአንድ ጊዜ ሶስት ቅርሶችን በመንግስታቱ ድርጅት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባሕል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በዓለም ቅርስነት ማስመዝገቧ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
ይህም ለሀገር ገፅታ ግንባታ፣ የመስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅና ለማልማት እንዲሁም ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
ዩኔስኮ ዕውቅና ለሰጣቸውም ሆነ ገና ላልተመዘገቡ ቅርሶች ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ የግሉ ዘርፍ እና ማህበረሰቡ ቅርሶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማሻገር ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
በቅርስ ጥገና ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ችግሩን ለመቅረፍ የስልጠና አማራጮችን ማስፋት ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል።