ቀጥታ፡

ስምምነቱን በሰጥቶ መቀበልና የቀጣናውን ትብብር በሚያጠናክር መልኩ መፈጸሙ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው-ምሁራን 

ዲላ/ድሬዳዋ፤ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፡-  ስምምነቱን በሰጥቶ መቀበል መርህና የቀጣናውን ትብብር በሚያጠናክር መልኩ  መፈጸሙ የሚኖረው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በቀጠናው ሀገራት መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባም ተመላክቷል። 

ከሌሎች አካላት ጋር የባህር በርን ለማግኘት የሚደረጉ ስምምነቶችን በሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲከናወኑ ማድረግ የተለመደና እንግዳ ያልሆነ ተግባር ነው።

በሰጥቶ መቀበል መርህ በሚከናወኑ ስምምነቶች ውስጥ የባህር በር የሌለው አገር አጠገቡ ወይም በአቅራቢያው ከሚገኝ ሌላኛው አካል ጋር ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ጥቅሞችን በማቅረብ የባህር በር የሚያገኝበትን ዕድል ያመቻቻል።

አገራችንም በዚሁ መርህ መሰረት ሰሞኑን  የባሕር በር የማግኘት የመግባቢያ ስምምነትን ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራርማ ወደ ተግባር ለመቀየር በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች።  

  ጉዳዩን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዲላና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራንም ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተከናወነና ለአካባቢውም አዲስ ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጥን የሚያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሱራፌል ጌታሁን እንደገለፁት፤ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በአንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው። 

ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት በማጋራት በምትኩ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል። 

የቀጣናውን ሰላምና መረጋጋት ታሳቢ ያደረገ ስምምነት ሊሆን እንደሚገባ ያነሱት ተመራማሪው ስምምነቱ ከሰጥቶ መቀበል መርህ ባለፈ የቀጠናውን ትብብር በሚያጠናከር መልኩ ሊተገበር እንደሚገባም አስረድተዋል። 

በቀጠናው የአንድ ሀገር ሰላምና ልማት ከጎረቤት ሀገራት ጋር የተሳሰረ ነው ያሉት ተመራማሪው ስምምነቱ  በቀጠናው አዲስ እድል ይዞ የሚመጣና ዘላቂ ሰላምና ልማትን በሚያረጋገጥ መልኩ ለመተግበር መስራት ይገባል ብለዋል። 

በተለይ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እውን እንዲሆን በቀጠናው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ሊገጥሙን የሚችሉ ተግዳሮቶችን ማስወገድ ይገባል ብለዋል።  

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር አብዱ መሃመድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የባህር በርን የማግኘት ጥያቄን ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለ ኢትዮጵያዊ የሃገሩ ዲፕሎማት ሊሆን ይገባል። 

መንግስት የጀመረው ቁርጠኛ አቋም በምሁራንም ሊደገፍ እንደሚገባ ገልጸው ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የባህር በርን የማግኘት የመግባቢያ ሰነድ የሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም