የኢትዮ-ሶማሊላንድ የባህር በር ስምምነት በቅንነት የሚወሰድና የሚደገፍ ሀገራዊ አጀንዳ ነው-የሀረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ሶማሊላንድ የባህር በር ስምምነት በቅንነት የሚወሰድና የሚደገፍ ሀገራዊ አጀንዳ ነው-የሀረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት
ሀረር፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ):- የኢትዮ-ሶማሊላንድ የባህር በር ስምምነት በቅንነት የሚወሰድና የሚደገፍ ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑን የሀረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የጋራ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የሚሻ በመሆኑ፤ በመንግሥት የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።
የጋራ ምክር ቤቱ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የሀረሪ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የተሰጠ መግለጫ።
የሀገርን ልማትና የህዝብን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ካለ ባህር በር ማሳካት አዳጋች ነው።
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የባሕር በር ባለቤትነት መብት ያላት ቢሆንም ለረጅም ዓመታት ከቀይ ባህር ጋር ያላት ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ግንኙነት ተቋርጦ ወደብ አልባ በመሆን ሀገራዊ የመበልጸግ ተስፋዋ በሌሎች በጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር ስምምነት በቅንነት የሚወሰድ ሀገራዊ አጀንዳ ነው።
ኢትዮጵያ በአለማችን ላይ ባህር አልባ ከሆኑ 44 ሀገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላት ሀገር ነች። ከዚህ በተጨማሪም ከባህር በቅርብ ርቀት ላይ ሆና የባህር በር የሌላት ቀዳሚዋ ሀገር በመሆንም ለአመታት የበይ ተመልካች ሆና ቆይታለች።
ሀገራችን ምንም እንኳን ቀደም ሲል የባህር ባለቤት የነበረች እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር ብትሆንም ላለፉት ሶስት አስርት አመታት ባህር አልባ ሆና መተንፈሻ ሳይኖራት ቆይታለች።
በተለይም በወጪና ገቢ ምርቶችን ለማጓጓዝ በሌላ ሀገር ጥገኛ መሆኗም በርካታ ኢኮኖሚ ጉዳት እያስከተለ ሲሆን በየአመቱ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ለወደብ ኪራይ ታወጣለች።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ወደብ አልባ በመሆኗ በዋናነትም የውጭ ምንዛሬን በማቀጨጭ ኢኮኖሚያዊ እድገቷ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት ካላት ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላትና ካላት የመልማት ፍላጎት አንፃር ካለ ባህር በር ውጭ አስገዳጅ እንዲሆን አድርጎታል።
ለኢትዮጵያ የባህር በር አስፈላጊነትና ለቀጣናዊ የልማት ትስስር ስምምነቱ የሚኖረውን ሚና በግልጽ የተረዳንበት ነው።
የመግባቢያ ስምምነቱ ዙሪያ የተሰጠው ማብራሪያ የሚሰሙ ብዥታዎችን የሚያጠራ ብሎም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመቆም የሚያስችል ነው።
የጋራ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የሚሻ በመሆኑ፤ በመንግሥት የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።
የሀረሪ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት
ጥር 3 ቀን 2016 ዓ/ም
ሀረር