በኢትዮጵያ ወቅታዊና ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ወቅታዊና ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ወቅታዊና ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃዎችን ተደራሽነት ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋልና የባለሙያዎች አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ማድረጉን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ በ2016 የበልግ ወቅት በሚኖረው ወቅታዊ የአየር ጠባይ ትንበያ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ውይይት እያካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያምን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ትንበያዎችና መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ በኩል በትኩረት እየተሰራ ነው።
ለዚህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም ባለፈ ቀጣይነት ያለው የባለሙያ አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።
አቶ ፈጠነ አክለውም በዘንድሮው በጋ የተሰጠው ወቅታዊ የትንበያ መረጃ በአሁኑ ወቅት መሬት ላይ እየታየ ካለው የአየር ጠባይ ጋር የተጣጣመ ሲሆን ይህም ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የታዩበት ነው ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው የዓለም አቀፍ አየር ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ወቅታዊ ትንበያዎች ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸው አብራርተዋል።
ከዚህ አኳያ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ሂደት ኢንስቲትዮቱ የጀመራቸውን ስራዎች ሊያጠናክር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም መገናኛ ብዙሃን ድርቅን ጨምሮ የተለያዩ አደጋዎች ሲደርሱ ከመዘገብ ባለፈ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን በየወቅቱ ተደራሽ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።