ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞች ከንቲባዎች እና ባለድርሻ አካላት ለስራ ጉብኝት ድሬዳዋ ገቡ

ድሬዳዋ ፤ ጥር 3/2016 (ኢዜአ)፦ ከ80 በላይ የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ከንቲባዎች እና የክልሎች የከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ አመራሮች በድሬዳዋ የስራ ጉብኝትና የልምድ ልውውጥ ዐውደ ጥናት ያካሄዳሉ።

ከ80 በላይ የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ከንቲባዎች እና የክልሎች የከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ አመራሮች በድሬደዋ የስራ ጉብኝትና የልምድ ልውውጥ ለማካሄድ ዛሬ ድሬዳዋ ገብተዋል።

ከንቲባዎቹ በድሬደዋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁንና የካቢኔ አባላት አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ከንቲባዎቹና ባለድርሻ አካላቱ የተካተቱበት የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ  ዛሬና ነገ በመስክ ጉብኝት የተደገፈ የልምድ ልውውጥና ዐወደ ጥናት ያካሂዳሉ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ የልምድ ልውውጡና ዐወደ ጥናቱን ያዘጋጀው የኢፌዴሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ጋር በመቀናጀት ነው።

በዐውደ ጥናቱና የልምድ ልውውጡ በከተማ መሬትና ካዳስተር፣ በከተማ ፕላን፣ በከተማ አመራርና ፋይናንስ ስራዎች እና በማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች አሰባሰብ ላይ ልምድ የሚሆኑ የስራ አፈፃፀሞች ይለያሉ ብለዋል።

በተለይም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር  የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰብ ላይ ያለው ልምድና ተሞክሮ  በዐውደ ጥናት መድረኩ ላይ የሚቀርብ ይሆናል።

የከተማው የመሬት ፋይል አደረጃጀት ማኔጅመንት ልምድ በመስክ  እንደሚደረግም ጨምረው ተናግረዋል ።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚሁ ዐወደ ጥናትና የስራ ጉብኝት ላይ ከ80 በላይ ከተሞች ከንቲባዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የስራ ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም የክልሎች የከተማ መሬትና ፕላን ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ኢዜአ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም